ቀጥታ፡

የአፍሪካ ቀንድ ሀገራትን የንግድ አቅም የሚያሳድግ የ83 ሚሊዮን ዩሮ ስምምነት ተፈረመ 

አዲስ አበባ ፤ታህሳስ 8/2016  (ኢዜአ)፦ የአፍሪካ ቀንድ ሀገራትን የንግድ ፋይናንስ አቅም የሚያሳድግ የ83 ሚሊዮን ዩሮ ስምምነት መካሄዱ ተገለጸ።

የአፍሪካ ቀንድ ኢንሼቲቭ 19ኛው የሚኒስትሮች ስብሰባ የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴን ጨምሮ አውሮፓ ህብረት ምክትል ፕሬዚዳንት ማርጋሪታስ ስኪናስ እንዲሁም የአባል ሀገራቱ ሚኒስትሮች በተገኙበት በብራሰልስ ተካሂዷል።

በስብሰባው ዓለም አቀፍ የፋይናንስና ልማት ተቋማት ለቀጠናው ሀገራት የሚያደርጉትን ድጋፍ ስለሚያሳድጉበት ሁኔታ ምክክር የተደረገ ሲሆን የፋይናንስ ዲጂታል ፖሊሲ ፍኖተ ካርታ ስለሚተገበርበት ሁኔታም መወያየታቸው ተመልክቷል።

የአፍሪካ ቀንድ ኢንሼቲቭ የወቅቱ ሊቀ መንበርና የኢትዮጵያ  ገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ የአፍሪካ ቀንድ ኢንሼቲቭ   አባል ሀገራት  መብዛት  በሀገራቱ መካከል የንግድ  ትስስርና ተጠቃሚነት ያሳድገል ብለዋል።

 ኢንሼቲቩን አዲስ የተቀላቀለችው ዩናይትድ ኪንግደምም ለዘርፉ እድገት ተጨማሪ አቅም እንደምትሆን ተናግረዋል።

የአውሮፓ ሕብረት ምክትል ፕሬዚዳንት ማርጋሪታስ ስኪናስ ሕብረቱ የኢኒሼቲቩን አቅምና የቀጠናውን የንግድ ፋይናንስ ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረው በአፍሪካ ቀንድ የግል ኢንቨስትመንቶችን ለመሳብ እንዴት የዲጂታል ፋይናንስ ስርዓትን መዘርጋት ይገባል የሚለው የስብሰባው አጀንዳ መሆኑን አውስተዋል። 

ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን፣ የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ እና የአውሮፓ ህብረት ግሎባል ጌትዌይ በአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ በኩል በቀጠናው የፋይናንስ ድጋፍ እንዲያደርጉ የሚያስችል ምከረ ሀሳብ መነሳቱም ተመልክቷል።

በዚህም የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት የንግድ ፋይናንስ አቅምን የሚያሳድግ የ83 ሚሊዮን ዩሮ ስምምነት መካሄዱ ተገልጿል።

ስምምነቱ በቀጠናው የሚተገበሩ የንግድ ልማቶችን ለማጎልበት ከፍተኛ አቅም እንደሚኖረውም መነሳቱን ከገንዘብ ሚኒሰቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም