ቀጥታ፡

በክልሉ የሚገኘውን የተፈጥሮ ደን አልምቶ ህብረተሰቡን ከካርቦን ሽያጭ ተጠቃሚ የማድረግ ተግባር እየተከናወነ ነው

ቦንጋ ፤ታህሳስ 8/2016 (ኢዜአ)፦ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የሚገኘውን የተፈጥሮ ደን በአግባቡ በመጠበቅ ከካርቦን ሽያጭ ተጠቃሚ ለመሆን እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ደን፣ አካባቢ ጥበቃ እና አየር ንብረት ለውጥ ቁጥጥር ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ኃላፊ ዶክተር አስራት መኩሪያ እንዳሉት፤ የክልሉ ማህበረሰብ የተፈጥሮ ደንን ለዘመናት ጠብቆ ያቆየ ቢሆንም ከዘርፉ ማግኘት የሚገባውን ጥቅም ሳያገኝ ቆይቷል።

በህዝቡ ቁጥር መጨመር፣ ከስራ አጥ ወጣቶች ቁጥር መበራከትና ከሌሎች ጉዳዮች ጋር ተያይዞ በተፈጥሮ ደን ላይ ጉዳት እየደረሰ በመሆኑ ይሄን ችግር ለመቅረፍ  ህብረተሰቡን ከካርበን ሽያጭ ተጠቃሚ ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነም ተናግረዋል።

በክልሉ የሚገኙ ሁለት የባዮስፌር ጥብቅ ሃብቶችን ፍቃድ የማደስና የካርቦን ክፍያ ስራን ለመስራት የፕሮጀክት ንድፈ ሃሳብ በማዘጋጀት ከተለያዩ የፌደራል ተቋማትና አለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

ከዚህ መነሻ የስፔስ ሳይንስና ጂኦ እስፓሺያል ኢንስቲትዩት ጥያቄውን ተቀብሎ የሰው ሀይልና ሀብት መድቦ የፕሮጀክት ፕሮፖዛል ማቅረቡን ጠቁመዋል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ በበኩላቸው ክልሉ ለረጅም ዘመናት ደንን በባህላዊ መንገድ ጠብቆ ያቆየ ማህበረሰብ የሚገኝበት መሆኑን ገልፀዋል።


 

ህብረተሰቡ ደኑን ጠብቆ ያቆየውን ያህል ተጠቃሚ ካለመሆኑ ጋር ተያይዞ የተለያዩ ጥያቄዎችን ሲያነሳ መቆየቱንም ተናግረዋል።

ይሄን ጥያቄ መሰረት በማድረግ ህብረተሰቡን ከካርቦን ሽያጭ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል በጥናት ላይ የተመሠረተ ስራ ለመስራት በተደረገው እንቅስቃሴ ዉስጥ የኢትዮጵያ ጂኦ እስፓሺያል ኢንስቲትዩት ላደረገው አስተዋጽኦ አመስግነዋል።

በኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎች ከካርቦን ሽያጭ ተጠቃሚ መሆናቸውን ያነሱት ዶክተር ኢንጅነር ነጋሽ የክልሉን ህብረተሰብም ከዚህ ተጠቃሚ ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ ጠቁመዋል።

በቀጣይ ስራውን ውጤታማ ለማድረግ ከኢንስቲትዩቱ ጋር በመተባበር የክልሉን የሰው ሀይል የማብቃት ስራ እንደሚሰራም ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም