ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ተጨማሪ  የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶችን ለማስመዝገብ የሰነድ ዝግጅቶችን እያጠናቀቀች ነው

አዲስ አበባ ፤ ታህሳስ 8/2016 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ተጨማሪ  የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶችን ለማስመዝገብ የሰነድ ዝግጅቶችን እያጠናቀቀች መሆኑን  የኢትዮጵያ የቅርስ ባለስልጣን አሰታወቀ።  

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው በ2016 ዓ.ም በዩኔስኮ የተመዘገቡ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶችን አስመልክተው ለመገናኛ ብዙሃን ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ከህዳር 24 እስከ ህዳር 29 ቀን 2016 ዓም በቦትስዋና ካሳኔ ከተማ በተካሔደው 18ኛው የማይዳሰሱ ቅርሶች ጥበቃ ጉባኤ ላይ የሓረሪ ብሔረሰብ የሹዋሊድ ክብረ በዓል በማይዳሰስ ቅርስነት መመዝገቡን ጠቅሰዋል። 

በተመሳሳይ በዚሁ ዓመት የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ እና የጌዴኦ ባህላዊ መልክዓ ምድርን በዓለም ቅርስነት ማስመዝገብ መቻሉን ገልጸዋል።

ቅርሶቹ የቱሪዝም ልማትን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ የሚያግዙ ቢሆኑም ኢትዮጵያ ካሏት ተፈጥሯዊና ታሪካዊ ሃብቶች አኳያ በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡት ጥቂቶቹ ናቸው ብለዋል፡፡

በቀጣይ የመልካ ቁጡሬ መካነ ቅርስን እኤአ በ2024 በማይዳሰስ ቅርስነት ለማስመዝገብ የሚያስችል የልየታና የሰነድ ዝግጅት ተጠናቆ ለሚመለከተው አካል መላኩን አስረድተዋል።

ሌላው በ2024 የሚዳሰስ ቅርስ ውስጥ ለማስመዝገብ እየተሞከረ ያለው የኢሳ ባህላዊና አፋዊ የህግ ስርዓት መሆኑን ጠቁመዋል።

የኢሳ ስርዓት ከሶስት የምስራቅ አፍሪካ አገራት ጋር በመተባበር የጋራ ቅርስ እንዲሆን ለማስመዝገብ ጥረት የሚደረግ መሆኑን ተናግረዋል።

የጋራ ቅርሱ የምዝገባ ሂደት በኢትዮጵያ ፣ በሶማሊያና በጁቡቲ መካከል የሚከናወን ሲሆን የሰነድ ዝግጅቱን ኢትዮጵያ በባለቤትነት እያከናወነች ስለመሆኑም አስረድተዋል።

በአለም ቅርስነት የተመዘገቡት የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ሃብቶች የውጭ ጎብኚዎችን ለመሳብ ዕድል የሚፈጥሩ መሆናቸውን ዋና ዳይሬክተሩ አንስተዋል።

በተጨማሪም አገሪቱ ያሏትን ተፈጥሯዊና ታሪካዊ ሃብቶች በማልማት የኢኮኖሚ ተጠቃሚነቷን እንድታሳድግ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ያግዛል።

ቀደም ሲል የደመራና የጥምቀት በዓል እንዲሁም የፊቼ ጨምበላላና የገዳ ባህላዊ አስተዳደር በማይዳሰስ ቅርስነት መመዝገባቸው ይታወቃል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም