ቀጥታ፡

ሀገራዊ ወጪን በሀገር ውስጥ ገቢ ለመሸፈን የታክስ ምርመራና ኦዲት ስራዎች ከፍተኛ ሚና አላቸው - የገቢዎች ሚኒስቴር

አዲስ አበባ ፤ ታህሳሥ 8/2016 (ኢዜአ)፦ ሀገራዊ ወጪን በሀገር ውስጥ ገቢ ለመሸፈን በሚደረገው ጥረት የታክስ ምርመራና ኦዲት ስራዎች ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው የገቢዎች ሚኒስትር  አይናለም ንጉሴ ገለጹ።

የታክስ ምርመራና ኦዲት ስራን በተጠናከረ መልኩ መተግበር ሀገሪቱ ማግኘት ያለባትን ገቢ እንድታገኝ ከማድረጉም በላይ ታክስ ከፋዮች ህጋዊ አሰራርን እንዲከተሉ ያደርጋል ብለዋል፡፡

ሚኒስቴሩ የታክስ ምርመራና ኦዲት ሽፋንን ለማሳደግ የሚያደርገውን ጥረት ለመደገፍ በተለያዩ ቅርንጫፎች ይሰሩ የነበሩ ባለሙያዎችን ከፍተኛ የሥራ ጫና ወደ ሚስተዋልባቸው ቅርንጫፎች ለማሰማራት ኦረንቴሽንና የስራ ስምሪት ሰጥቷል፡፡


 

በመድረኩ ተገኝተው የስራ ስምሪት የሰጡት የገቢዎች ሚኒስትር  አይናለም ንጉሴ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እንደ ሀገር ከፍተኛ ኃላፊነት እንደተጣለበት ገልጸዋል።

በዚህም መላው የመስሪያ ቤቱ አመራርና ሠራተኞች ባደረጉት ጥረት ባለፉት አምስት ዓመታት ከፍተኛ ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል፡፡

ይህንን ውጤት ለማስቀጠል ከሌሎች ተግባራት ጎን ለጎን የኦዲት ሽፋንን ማሳደግ ያስፈልጋል ሲሉም ሚኒስትሯ አክለዋል።

እንደ ሀገር የሚያስፈልገውን የበጀት ፍላጎትና የሚሰበሰበውን ገቢ ለማጣጣም ተቋሙ በትኩረት እየሰራ ይገኛል ነው ያሉት፡፡

ባለሙያዎቹ በሚኖራቸው የስራ ቆይታ የተጣለባቸውን ሀገራዊ ግዴታ እንደሚወጡና በየቅርንጫፎች ከሚገኙ ባለሙያዎች የተሻለ ልምድ እንደሚቀስሙ ገልጸዋል፡፡


 

በሚኒስቴሩ የታክስ ሥርዓት ዘርፍ ሚኒስትር ደኤታ አቶ ተስፋዬ ቱሉ በበኩላቸው የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በሚያመነጨው ልክ የሚፈለገው ገቢ እየተሰበሰበ አለመሆኑን ጠቅሰዋል።

በበጀት ዓመቱ የተያዘውን 529 ቢልዮን ብር ገቢ ለማሳካት የታክስ አሰባሰባችንን ማዘመንና የሚፈለገውን ገቢ ለመሰብሰብ ካለፈው ክረምት ጀምሮ ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡

ከስራዎቹ መካከል የታክስ ኦዲት ሽፋንን ማሳደግ አንዱ መሆኑን ጠቀሰው ባለሙያዎቹም የተጣለባቸውን የሥራ ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ ማሳሰባቸውን ከገቢዎች ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም