በጊኒ ነዳጅ ማጠራቀሚያ ስፍራ ላይ በተከሰተ ፍንዳታ የሰዎች ሕይወት አለፈ

385

አዲስ አበባ ፤ ታህሳሥ 8/2016 (ኢዜአ)፦ በጊኒ ዋና ከተማ ኮናክሬ በነዳጅ ማጠራቀሚያ ስፍራ ላይ በተከሰተ ፍንዳታ ቁጥራቸው ያልታወቁ ሰዎች ሕይወት ማለፉና ከፍተኛ ጉዳት መድረሱ ተገልጿል። 

ኮናክሬ በሚገኘው ግዙፍ የነዳጅ ማደያ ዛሬ ሌሊት ከፍተኛ ፍንዳታ መከሰቱንና እስካሁንም መቆጣጠር እንዳልተቻለ ቢቢሲ በዘገባው አስነብቧል።

የአይን እማኞች ለሮይተርስ በሰጡት መረጃ ደግሞ ቁጥራቸው ያልታወቁ ሰዎች ለህልፈት ሲዳረጉ ሌሎች ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

አደጋው በደረሰበት አካባቢ የሚገኙ ተቋማትም ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው የተነገረ ሲሆን ብዙዎች ከአካባቢው በመሸሽ ላይ መሆናቸው ተመልክቷል።

የአደጋ መከላከል እና ወታደራዊ ባለሙያዎችን ዋቢ አድርጎ የዘገበው ሮይተርስ ኢግናሴ ዲን እንዲሁም ዶንካ የተባሉት ሆስፒታሎች በቁስለኞች መጨናነቃቸውን አመልክቷል።

በነዳጅ ማጠራቀሚያው ላይ የተከሰተውን ፍንዳታ ለመቆጣጠር የጊኒ ወታደራዊ ተቋማትና የእሳት አደጋ ሰራተኞች ርብርብ እያደረጉ ስለመሆኑም ዘገባው አስነብቧል። በመረጃው ስለ አደጋው መንስኤ ምንም የተባለ ነገር የለም። 

ዘግይተው በወጡ መረጃዎች ደግሞ  አደጋው ማየሉን ተከትሎ ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸውን ተጠቁሟል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም