የህብረት ስራ ማህበራት መዋቅራዊና ተቋማዊ የለውጥ ስራ ውጤታማ እንዲሆን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይደገፋል -- ምክትል አፈ ጉባኤ ሎሚ በዶ - ኢዜአ አማርኛ
የህብረት ስራ ማህበራት መዋቅራዊና ተቋማዊ የለውጥ ስራ ውጤታማ እንዲሆን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይደገፋል -- ምክትል አፈ ጉባኤ ሎሚ በዶ
አዳማ፤ ታህሳስ 8/2016(ኢዜአ )፡-የህብረት ስራ ማህበራት መዋቅራዊና ተቋማዊ የለውጥ ስራ ውጤታማ እንዲሆን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ድጋፉን እንደሚያጠናክር የምክር ቤቱ ምክትል አፈ ጉባኤ ሎሚ በዶ ገለጹ።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አመራሮችና የምክር ቤቱ ተጠሪ አመራሮች በህብረት ስራ ማህበራት የልማትና ዕድገት ሪፎርም ዙሪያ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ያለመ የምክክር መድረክ በአዳማ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
ዘርፉ በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ሪፎርም ማሻሻያ ውስጥ ወሳኝ ሚና እንዲኖረው የህብረት ስራ ልማትና ዕድገት ሪፎርም ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱ ተመልክቷል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሎሚ በዶ በመድረኩ ላይ እንደገለፁት የህብረት ስራ ማህበራት ጉልበት፣ ገንዘብና ዕውቀታቸውን በአንድ ላይ በማሰባሰብ እድገትን በማፋጠን ረገድ ወሳኝ ሚና አላቸው።
የግብርና ምርት ማሳደጊያ ግብዓትን በማቅረብና በማሰራጨት፣ የሸቀጦችና የአገልግሎት ገበያን በማረጋጋት፣ የቁጠባ ባህል እንዲጎለብት እንዲሁም በኢንቨስትመንት በመሳተፍ የተሻለ ስራ እየሰሩ መሆኑንም አንስተዋል።
ማህበራቱ የበለጠ ውጤታማ እንዲሆኑ የአደረጃጀት፣ ዘመናዊ የአሰራርና አመራር ማነቆዎችን ጨምሮ የክትትልና ቁጥጥር ስራዎችን ማጠናከር እንደሚገባ ገልጸዋል።
የተጀመረው ሪፎርምም ማህበራቱ የካፒታል አቅማቸውን ለማጠናከር፣ የቴክኖሎጂና አቅርቦት ድርሻቸውን ለማሳደግ፣ በሀገር ውስጥና በውጭ ገበያ የተወዳዳሪነት ሚናቸው እንዲጎለብት፣ የኢንቨስትመንት ተሳትፏቸው እንዲጠናከር ያስችላል ብለዋል።
በዘርፉ የሚደረገው የተቋማዊ፣ አደረጃጀት፣ አሰራርና የህግ ማዕቀፍ ማሻሻያዎች ውጤታማ እንዲሆኑ የምክር ቤቱ አባላትና አመራሮች ድጋፋቸውን ያጠናክራሉ ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ የህብረት ስራ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ጌታቸው መለስ በበኩላቸው ዘርፉ ሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያን መደገፍ እንዲችል በሀገር ውስጥና በውጭ ገበያ ተፅዕኖ ያላቸውና ተወዳዳሪ የህብረት ስራ ማህበራት ማፍራት አስፈልጓል ብለዋል።
በሀገሪቷ 59 ቢሊዮን ብር ካፒታልና 27 ሚሊዮን አባላት ያላቸው ከ106 ሺህ በላይ ማህበራትና ዩኒየኖች መኖራቸውን ጠቅሰው በብዛት ከምርት ማሳዳጊያ ግብዓት አቅራቢነትና በከተሞች ገበያ ማረጋጋት ላይ ብቻ አቅማቸው መወሰኑን ገልጸዋል።
ማህበራቱ የፋይናንስ አቅርቦት እጥረት እንዲሁም የቴክኖሎጂ፣ የዕውቀትና የክህሎት ክፍተቶች እንዳለባቸው ጠቅሰው የሚካሄደው ሪፎርም እነዚህን ችግሮች ጨምሮ የአደረጃጀት፣ የአሰራር፣ አገልግሎት አሰጣጥና የሀብት ብክነት ችግሮችን መቅረፍ ያስችላል ብለዋል።
በተጨማሪም የአመራርና የአስተዳደር ስርዓታቸውን በማሻሻል በሰለጠነ የሰው ሃይልና ወጥ በሆነ አሰራርና አደረጃጀት እንዲመሩ ለማድረግ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።