ኢትዮ ኢንጅነሪንግ ግሩፕ የላዳ ተሽከርካሪዎችን በኢትዮጵያ መገጣጠም ሊጀምር ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮ ኢንጅነሪንግ ግሩፕ የላዳ ተሽከርካሪዎችን በኢትዮጵያ መገጣጠም ሊጀምር ነው

አዲስ አበባ ፤ ታህሳስ 7/2016 (ኢዜአ)፦ኢትዮ ኢንጅነሪንግ ግሩፕ የላዳ ተሽከርካሪዎችን በኢትዮጵያ መገጣጠም የሚያስችለውን የፍላጎት ሰነድ ስምምነት ከሩሲያው ላዳ ኩባንያ ጋር ተፈራርሟል፡፡
ስምምነቱን የኢትዮጵያ ኢንጅነሪንግ ግሩፕ ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ሱሌማን ደደፎና የላዳ ኩባንያ የሽያጭና ገበያ ምክትል ፕሬዝዳንት ኢሊያ ሳቪኖቭ ተፈራርመዋል።
አምባሳደር ሱሌማን ደደፎ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የፍላጎት ስምምነቱ የላዳ ኩባንያ ምርት የሆኑ ተሽከርካሪዎችን በኢትዮጵያ መገጣጠም የሚያስችል ነው።
በዚህም በቀጣይ ጥቂት ወራት ውስጥ ስምምነቱን ተግባራዊ እንደሚደረግም ነው የተናገሩት፡፡
ምርቶቹ በዋናነት ለአገር ውስጥ ገበያ የሚውሉ ሲሆን፤ በሂደትም ወደ ሌሎች የአፍሪካ አገራት እንደሚቀርቡ አስረድተዋል፡፡
ስምምነቱ የሁለቱ አገራትን የኢኮኖሚ ትስስር ለማጠናከር ሚናው የጎላ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡
የላዳ ኩባንያ የሽያጭና ገበያ ምክትል ፕሬዝዳንት ኢሊያ ሳቪኖቭ በበኩላቸው በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ጠንካራ ወዳጅነት በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ እድል መፍጠሩን ጠቁመዋል፡፡
የሩሲያው ላዳ ኩባንያ የ50 ዓመታት ተሽከርካሪ የማምረት ልምድ ያለው ኩባንያ መሆኑ ይታወቃል፡፡