ቀጥታ፡

ኮሚሽኑ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አጀንዳ የሚሰጡ የማህበረሰብ ክፍል ተወካዮች መረጣ ማከናወን ሊጀምር ነው 

ሆሳዕና ፤ታህሳስ 7/2016 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አጀንዳ የሚሰጡ የማህበረሰብ ክፍል ተወካዮች መረጣ ማከናወን ሊጀምር መሆኑን አስታወቀ። 

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ሙልጌታ አጎ ለመገናኛ ብዙሃን ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንደገለጹት፤ ኮሚሽኑ በአምስት ክልሎችና ሁለት የከተማ አስተዳደሮች የተሳካ የተሳታፊዎች ልየታና የተወካዮች መረጣ ማከናወን ችሏል።

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልልም ከዚህ ቀደም ባሰለጠናቸው ተባባሪ አካላት አማካኝነት ከየማህበረሰብ ክፍሉ አጀንዳ የሚሰጡ ሰዎችን መረጣ እንዲያከናውኑ አቅጣጫ መቀመጡን ጠቁመው፤ ከነገ ታህሳስ 8 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በአምስት ቀናት ውስጥ የመረጣ ሥራ እንደሚጀምር ተናግረዋል። 

በክልሉ በሚገኙ ሁሉም መዋቅር አጀንዳ የሚሰጡ የማህበረሰብ ክፍሎችን በኮሚሽኑ በተቀመጠው መስፈርት መሰረት መረጣው እንደሚከናወን አብራርተዋል።

አጀንዳ ከሚሰጡ የማህበረሰብ ክፍሎች ውስጥ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ ንግዱ ማህበረሰብ፣ መምህራን፣ አርሶ አደሮች፣ ማህበረሰብ መሪዎች፣ የመንግስት ሰራተኞች እንደሚገኙበት ጠቁመዋል።

የተወካዮቹ የመረጣ ሂደትም አካታችነት፣ አሳታፊነትና ግልፀኝነት ላይ የተመሰረተ መሆኑን ጠቁመው፤ እንደ አገር ለታሰበው የምክክር ሂደትና ስኬት አመርቂ ውጤት ለማስመዝገብ የሚያግዝ መሆኑን አብራርተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም