ጅማን የሚጎበኙ ቱሪስቶች ቁጥር እየጨመረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ጅማን የሚጎበኙ ቱሪስቶች ቁጥር እየጨመረ ነው

ጅማ፤ህዳር 07/2016 (ኢዜአ)፡- በጅማ ከተማና አካባቢዋ የሚገኙ የቱሪስት መስህቦችን የሚጎበኙ ቱሪስቶች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን የከተማው ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
ወደ ከተማዋ የሚመጡ ጎብኚዎችን ቆይታ የተመቻቸ ለማድረግና የከተማዋን የቱሪዝም ገቢ ከፍ ለማድረግ ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑም ተገልጿል።
ጅማ ከተመሰረተች ሁለት ምዕተ ዓመት የሚጠጋት ሲትሆን የቀደምት ነገስታት ታሪክ ባለቤትና የጥንታዊ ንግድ መስመር በመሆኗ የጎብኚዎችን ቀልብ የሚስቡ በርካታ ቅርሶች አሏት።
ጅማ በሙዝየሟ ውስጥ ካሏት ድንቅ ቅርሶቿ በተጨማሪ የአካባቢው ባህላዊ እሴቶች የታደለች ነች።
የጅማ ከተማ የባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ነጂብ ራያ እንዳሉት የቱሪስት ፍሰቱን በማሳደግ የቱሪዝም ገቢን ለማሳደግ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ ነው።
ለቅርሶች የሚደረገው ጥገና፣ ጥበቃና እንክብካቤ፣ የከተሞቹን መዳረሻ መንገዶችና የሆቴሎችን ደረጃዎች ማሳደግ እንዲሁም በከተማው ወንዞች ዳርቻ ላይ እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን እንደ አብነት በማንሳት።
ጅማን ባለፈው ዓመት 4ሺህ 643 ቱሪስቶች የጎበኙ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 103 የውጭ ሀገር ቱሪስቶች መሆናቸውን አንስተዋል።
ከዚህም ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን አንስተው፤ በያዝነው ዓመት ባለፉት አምስት ወራት ብቻ ከአምናው ሙሉ ዓመት ጋር የሚስተካከል ቁጥር ያለው የጎብኚ መጠን ከተማዋንና አካባቢዋን መጎብኘታቸውን አክለዋል።
የንጉስ አባ ጅፋር ቤተመንግስትና ሙዝየም፣ ጥንታዊ መስጊዶች እና የነገስታቱ የመቃብር ስፍራዎች በከተማዋ ከሚገኙ ዋና ዋና የቱሪስት መስህቦች መካከል መሆናቸውንም ተናግረዋል።
ጅማን ሲጎበኙ ያገኘናቸው ቱሪስቶች በሰጡት አስተያየት "ጅማ የቀደምት አባቶቻችን ታሪክ የምንማርበት እና የዘመኑን የአኗኗር ሁኔታ የምንቃኝበት ከተማ ነው" ብለዋል።
ጅማ ሙዝየምን በመጎብኘት ላይ የነበረችው ተማሪ ሀረገወይን ኩምሳ በሰጠችው አስታያየት "ታሪካዊ ቦታዎችና ቅርሶችን ማየት ያስደስተኛል" ብላለች።
ታሪካዊ ቁሶችን እና የነገስታቱን አልባሳትና መገልገያ ዕቃዎች ስናይ በዘመኑ የነበረውን የአኗኗር ሁኔታና የስልጣኔ ደረጃ ለማወቅ ያግዘናል ብላለች።
ሌላው ጎብኚ ሃምሳ አለቃ አኑዋር መኮንን በበኩላቸው ጥንታዊ ቅርሶችን መጎብኘት "አባቶቻችን ያሳለፉትን ዘመን መለስ ብለን እንድንቃኝ እድል የሚሰጥ ነው" ብለዋል።
ንጉስ አባጅፋር ያስተዳደሩበት የነበረው የዳኝነት ስርዓት፣ ከሌሎች ነገስታት ጋር የነበራቸው መልካም ግንኙነት፣ ለዘመናዊ ስልጣኔ የከነበራቸውን ቀናኢ ፍላጎት ማየታቸውን በማከል።
የሀገርን ታሪክ ማወቅ እና መረዳት የአባቶችን ፈለግ ተከትለን ሀገራችንን እንድንወድና እንድናከብር የሚያደርግ በመሆኑ እንደነዚህ አይነት ቅርሶችን መጎብኘት ያስፈልጋል ነው ያሉት።