የአገር ባለውለታዎችን ያፈራውን የኢትዮጵያ አየር ኃይል በላቀ ብቃትና ጀግንነት ለማገልገል ተዘጋጅተናል - የአየር ኃይል ተመራቂ መኮንኖች - ኢዜአ አማርኛ
የአገር ባለውለታዎችን ያፈራውን የኢትዮጵያ አየር ኃይል በላቀ ብቃትና ጀግንነት ለማገልገል ተዘጋጅተናል - የአየር ኃይል ተመራቂ መኮንኖች
አዲስ አበባ ፤ ታህሳስ 7/2016 (ኢዜአ)፦ የሀገራቸውን ክብር ያስጠበቁ ጀግኖችን ያፈራውን የኢትዮጵያ አየር ኃይል በላቀ ብቃትና ጀግንነት ለማገልገል መዘጋጀታቸውን በተለያዩ ዘርፎች ሰልጥነው የተመረቁ መኮንኖች ተናገሩ።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል 88ኛ ዓመት የምስረታ በዓል የማጠቃለያ ሥነ-ሥርዓት ትናንት በቢሾፍቱ አየር ኃይል ጠቅላይ መምሪያ ተካሄዷል።
በመርኃ-ግብሩ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች አየር ኃይል አባላት ከኢትዮጵያ አየር ኃይል ጋር በመሆን “ጥቁር አንበሳ" የተሰኘ የአየር ትርዒት አከናውነዋል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል ያሰለጠናቸው አብራሪዎች፣ የበረራ አስተማሪዎች፣ ቴክኒሻኖችና የነገ የአየር ኃይል መሪ ኦፊሰሮችን አስመርቋል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ተመራቂ መኮንኖች የኢትዮጵያ የአየር ክልልን በብቃት በማስከበር ላይ የሚገኘው አየር ኃይል አባል በመሆናቸው ትልቅ ኩራት እንደሚሰማቸው ተናግረዋል።
ከተመራቂዎቹ መካከል የዋንጫ ተሸላሚው ምንተስኖት ታደሰ የአገር ትልቅ ሀብት በሆነው የኢትዮጵያ አየር ኃይል የተሰጠኝን ሃላፊነት በብቃት ለመወጣት ዝግጁ ነኝ ብሏል።
የውትድርና ስልጠና ብዙ ዕውቀትና ልምድ የሚገኝበት መሆኑን በመግለጽ ሌሎች ወጣቶች ዘርፉን በመቀላቀል አገራቸውን እንዲያገለግሉ ጠይቋል።
ሌላኛዋ ተመራቂ መኮንን ደብረወርቅ የኔሰው መከላከያ ሰራዊት የሀገር ምሽግ እንደሆነ በመግለጽ የሰራዊቱ አባል በመሆኗ ኩራት እንደሚሰማት ተናግራለች።
አየር ኃይል የኢትዮጵያን የአየር ክልል በብቃት በማስከበር ላይ የሚገኝ ታላቅ ተቋም መሆኑንም ጠቅሳለች።
እንደ አየር ኃይል ባሉ የአገር ኩራት የሆኑ ተቋማት ውስጥ መሰልጠንና አገርና ህዝብን ማገልገል ደግሞ መታደል ነው ብላለች።
ካዴት ዋንጋሪ አበራ በበኩሏ ብዙ ፈተናዎችን በመቋቋምና የሚፈለገውን መሥዋዕትነት በመክፈል ግብን ማሳካት እንደሚገባ ተናግራለች።
የአየር ኃይሉ ከአፍሪካ ባለፈ የሰለጠነው ዓለም የደረሰበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ የሚጠበቅባትን ኃላፊነት እንደምትወጣ ገልጻለች።
የግራውንድ ኤሌክትሮኒክስ ተመራቂው ምክትል መቶ አለቃ ጃጃው አብርሃም የመከላከያ አባል በመሆንና ከፍተኛ ዕውቀት በመጨበጥ ራስን ማብቃት እንደሚቻል ተናግሯል፡፡
በቀጣይም ባገኘሁት ዕወቀት በመታገዝ አገሬን ወደ ፊት ለማራመድ በቁርጠኝነት እሰራለሁ ብሏል፡፡
የአየር ኃይሉ 88ኛ ዓመት የምስረታ በዓል "በመሥዋዕትነት ሀገርን የዋጀ፤ የኢትዮጵያ አየር ኃይል" በሚል መሪ ኃሳብ ከኅዳር 20 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ሲከበር ቆይቶ ትናንት ተጠናቋል።