ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር ኃይል እየገነባ ያለው አቅም ለአፍሪካ አብነት የሚሆን ነው-የተለያዩ አገራት ወታደራዊ አታሼዎች

አዲስ አበባ ፤ ታህሳስ 7/2016 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አየር ኃይል እየገነባ ያለው አቅም ለአፍሪካ አገራት ትምህርት የሚሰጥ መሆኑን በኢትዮጵያ የሚገኙ የተለያዩ አገራት ኤምባሲዎች ወታደራዊ አታሼዎች ገለጹ፡፡ 

የአፍሪካ አገራት የጋራ የጦር ልምምድን ጨምሮ በወታደራዊ ዘርፍ ያላቸውን ትብብር ማጠናከር እንዳለባቸውም ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር ኃይልና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች አየር ኃይል በጋራ "ጥቁር አንበሳ" የተሰኘ ልዩ የአየር ላይ ትርዒት ትናንት በቢሾፍቱ ከተማ አካሂደዋል፡፡

በኢትዮጵያ የተለያዩ አገራት ኤምባሲዎች የሚገኙ ወታደራዊ አታሼዎች በመርሃ ግብሩ ከታደሙት መካከል ይገኙበታል፡፡

በኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን ኤምባሲ ወታደራዊ አታሼ ብርጋዴር ጀነራል ጆክ አኖግ ዴንግ፤ በጋራ የጦር ልምምዱ እጅግ መደነቃቸውን ተናግረዋል፡፡

አፍሪካ አገራት መሰል የጋራ ትርኢቶችን በማስፋት በወታደራዊ ዘርፍ ያላቸውን ትብብር ማጠናከር እንደሚገባ ትምህርት የሰጠ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ 

ከሌሎች ወታደራዊ አታሼዎች ጋር በመሆን የኢትዮጵያ አየር ኃይል እያከናወናቸው ያሉ ስራዎች መጎብኘታቸውንም ጠቅሰው፤ በጉብኝታቸው በተመለከቷችው ስራዎች መደነቃቸውንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡



 

በኢትዮጵያ የሴኔጋል ኤምባሲ ወታደራዊ አታሼ ሌተናል ኮሎኔል ማማዱ ፋል በበኩላቸው በትርኢቱ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ያለውን ሙያዊ ብቃትና ቁርጠኝነት መመልከታቸውን ተናግረዋል፡፡

አየር ኃይሉ ያለበት ደረጃ እጅግ የላቀ መሆኑን መመልከታቸውንም ነው የተናገሩት፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም