ቀጥታ፡

ኢትዮጵያና ፓኪስታን በመገናኛ ብዙሃን ዘርፍ በትብብር ለመስራት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ተወያዩ

አዲስ አበባ ፤ ታህሳስ 7/2016 (ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያና ፓኪስታን በመገናኛ ብዙሃን ዘርፍ በትብብር መስራት በሚችሉበት ጉዳይ ላይ የሁለትዮሽ ውይይት አደረጉ ።

በእስላማዊ ሪፐብሊክ ፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር አብዱላ ከእስላማዊ ፓኪስታን ሪፐብሊክ የመረጃና መገናኛ ብዙሃን እንዲሁም የፓርላማ ጉዳዮች ተጠባባቂ ሚኒስትር ሙርታዛ ሶላንጂ ጋር በጉዳዩ ዙሪያ ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም በመረጃ እና በመገናኛ ብዙሃን ዘርፍ የጋራ ተጠቃሚነትና የሁለትዮሽ ትብብር ዙሪያ መምከራቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል።


 

የሁለቱን ሀገራት የባህልና ቱሪዝም ዘርፍ ለማስተዋወቅና በመረጃ ልውውጥ ላይ በትብብር መስራት የሚያስችል የትብብር ስራ ለመጀመር ፍላጎት እንደላቸው አምባሳደር ጀማል በከር ገልጸዋል።

የእስላማዊ ፓኪስታን ሪፐብሊክ የመረጃና መገናኛ ብዙሃን እንዲሁም የፓርላማ ጉዳዮች ተጠባባቂ ሚኒስትር ሙርታዛ ሶላንጂ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በኢኮኖሚው መስክ እያስመዘገበች ያለችውን ውጤት አድንቀዋል።

በተጨማሪም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)  የተነደፉ  መገናኛ ብዙሃን ዘርፍን ጨምሮ ሌሎች በሁለቱ ሀገራት መካከል ያሉትን የትብብር ግንኙነት ሊያጠናክሩ የሚችሉ   ኢኒሼቲቮች  በአረአያነት የሚጠቀሱ ናቸው ብለዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም