ከ60 በላይ ፍልሰተኞች የተሳፈሩበት ጀልባ በመሰበሩ በሜድትራኒያን ባሕር ውስጥ መስጠማቸው ተገለጸ

368

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 7/2016 (ኢዜአ)፡- ከሊቢያ ወደብ የተነሱ ከ60 በላይ ፍልሰተኞች የተሳፈሩበት ጀልባ በመሰበሩ ሜድትራኒያን ባሕር ውስጥ መስጠማቸውን የተባበሩት መንግስታት የፍልሰተኞች ድርጅት አስታወቀ።

አይ ኦ ኤም አንዳስታወቀው ፍልሰተኞቹ መነሻቸውን ሊቢያ በማድረግ የሜድትራኒያን ባሕርን በማቋረጥ ወደ አውሮፓ ለመግባት ሲሞክሩ በተነሳ ከፍተኛ ወጀብ ምክንያት ጀልባው በመሰበሩ እንደሰጠሙ  አስታውቋል።

ፍልሰተኞቹ ከናይጄሪ፣ ጋምቢያ እና ከሌሎች አፍሪካ ሀገራት የተነሱ ሲሆን ህጻናትና ሴቶች እንደሚገኙበትም ተመላክቷል።

ጀልባዋ ከተነሳችበት የሊቢያዋ ዙዋራ ወደብ 86 ሰዎችን አሳፍራ አንደነበር ከምንጮች ማረጋገጡን ድርጅቱ ይፋ ማድረጉን የሬውተርስ ዘገባ ያመላክታል።

ከጉዳቱ የተረፉ 25 ሰዎችም የህክምና ድጋፍ እየተደረገላቸው እንደሚገኝ በዘገባው ተመላክቷል።

የአይ ኦ ኤም ቃል አቀባይ ፈላቪኦ ዲጋካሞ እንዳሉት በያዝነው አመት ብቻ አደገኛውን የሜድትራኒያን ባህርን አቋርጠው ከአፍሪካ ወደ አውሮፓ ለመግባት የሞከሩ 2ሺህ 250 ሰዎች ህይወታቸው ማለፉን መግለጻቸውን ጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም