ቀጥታ፡

የጤና ተቋማት አክሪድቴሽን ፕሮግራምን ለማስጀመርና ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል የሶስትዮሽ ስምምነት ተፈረመ

አዲስ አበባ ፣ታህሳስ 7/2016 (ኢዜአ)፦የጤና ተቋማት አክሪድቴሽን ፕሮግራምን ለማስጀመርና ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል የሶስትዮሽ ስምምነት ተፈረመ።

የኢፌዴሪ ጤና ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ አክሪዲቴሽን አገልግሎትና የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት የጤና ተቋማት አክሪዲቴሽን ፕሮግራምን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል የሶስትዮሽ ስምምነት ተፈራርመዋል።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አየለ ተሾመ  አንዳሉት የአክሪዲቴሽን ስርዓት በተበታተነ መልኩ የሚተገበሩ ሪፎርሞችን በማቀናጀት ዘላቂነት ያለው የአገልግሎት ማሻሻያ ስራ ለመስራት ያስችላል ።

ትምህርት፣ አገልግሎት ሰጭ፣ ገዥና ተቆጣጣሪ ተቋማት  ለአንድ አላማ በመስራት  ተቋማዊ ባህልን በመቀየር ቀጠጠናዊና አለምአቀፋዊ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ ያግዛል  ብለዋል።

የተቋማት አክሪዲቴሽን የምላሽ ስርዓትን ማሻሻል፣ ቴክኖሎጂ መጠቀምና የሚጠበቁ ደረጃዎች መሆናቸውን አብራርተዋል።


 

የኢትዮጵያ አክሪዲቴሽን አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ቦንሳ ባይሳ በበኩላቸው መስሪያ ቤታቸው ከዚህ በፊት በተናጠል በላቦራቶሪ አክሪዲቴሽንና በተለያዩ አገልግሎቶች ዙሪያ የተወሰነ የነበረውን አሰራር ወደ  ጠቅላላ አገልግሎቶች  በማዞር  ተቋሙን አክሪዴት ወደ ማድረግ እንደሚሳድገው ገልፀዋል።

ይህም   ከዚህ በፊት ከህዝብ የሚነሱ የአገልግሎት ጥራት ጥያቄዎችን በመሰረታዊነት የሚፈታ ታሪካዊ ስምምነት እንደሚያደርገው ጠቁመዋል።

ከጤና ሚኒስቴር ጋር ደረጃዎችን በማውጣት ረዘም ያለ ልምድ እንዳላቸው የገለፁት ደግሞ የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሰረት በቀለ ናቸው።

 በጤናው መስክ የተዘጋጁ ከ100 በላይ ደረጃዎች መኖራቸውንና  በዘርፉ የተለያዩ ስልጠናዎችን እንደሚሰጥም  ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ጤና ክብካቤ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ዶክተር ማርቆስ ፈለቀ የሶስትዮሽ ስምምነቱ እስካሁን የመጣንበትን መንገድ የሚቀይርና የግልም ሆነ የመንግስት ጤና ተቋማት ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያበረታታ መሆኑን ጠቁመዋል።

የግል ጤና ተቋማት አበርክቷቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሆኑን የጠቀሱት ዶክተር ማርቆስ አክሪዲቴሽኑም እምነት የሚያተርፉበትና አንዱ ከአንዱ የሚለዩበት ሂደት በመሆኑ ጥቅሙ የጎላ መሆኑን አንስተዋል።

በመድረኩ ከኢትዮጵያ ትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን፣ ከገንዘብ ሚኒስቴር፣ ከጤና መድህን አገልግሎት፣ ከዓለም ጤና ድርጅት፣ ከተለያዩ አጋር ድርጅቶች እና ከባለድርሻ አካላት የተውጣጡ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል።

ተቋማቱ  ሀገር አቀፍ የጤና አክሪዲቴሽን ደረጃዎች  በጋራ እንደሚያዘጋጁ ና ድጋፍ  እንደሚደርጉ  መገለጹን ከጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለከታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም