በአማራ ክልል የተገኘው ሰላም ህዝቡን በማሳተፍ የተገኘ ውጤት ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል የተገኘው ሰላም ህዝቡን በማሳተፍ የተገኘ ውጤት ነው
ባህርዳር ፤ ታህሳስ 6 /2016(ኢዜአ) ፡- በአማራ ክልል አሁን ላይ የተገኘው ሰላም በህግ ማስከበሩ ሂደት ህዝቡን በማሳተፍ የተገኘ ውጤት መሆኑ ተገለጸ።
የብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ጽህፈት ቤት የ2016 በጀት ዓመት ያለፉት አምስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማና የቀሪ ወራት አቅጣጫ ዙሪያ በባህርዳር ከተማ የምክክር መድረክ ተካሄዷል።
በዚህ ወቅት የጽህፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ ይርጋ ሲሳይ እንዳሉት፤ በክልሉ አጋጥሞ የነበረውን የሰላም መታጣት ችግር በመከላከያ ሰራዊትና የክልሉ የፀጥታ ኃይል ድጋፍ መቀልበስ ተችሏል።
በዚህም በክልሉ አብዛኛው አካባቢዎች ሰላም በማስፈን ወደ ልማት ለመሸጋገር እድል እየተፈጠረ መምጣቱን ተናግረዋል።
በየደረጃው ያለው አመራርም ህዝቡን ያሳተፈ የውይይት መድረክ በማዘጋጀት ሰላምን የማስከበር ተግባር መከናወኑን ገልጸዋል።
የመንግስት ሰራተኛው፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ሴቶችና ወጣቶች መንግስት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ እንዲሳካ ሚናቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
የቀረበውን የሰላም ጥሪ ብዙዎቹ እየተጠቀሙበት መሆኑንና በቀሪ ቀናት ሌሎችም በተመሳሳይ መተግበራቸው በክልሉ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍንና ልማቱን እንዲፋጠን ፋይዳው የጎላ እንደሆነም አስታውቀዋል ።
በፓርቲው የደቡብ ጎንደር ዞን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መንበር ክፈተው በበኩላቸው፤ የቀረበው የሰላም ጥሪ ያጋጠመውን የጸጥታ ችግር ለመፍታት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ተናግረዋል።
በየደረጃው ህዝባዊ መድረኮችን በመፍጠር የተሻለ ለውጥ እንዲመጣ እየሰሩ መሆናቸውን አመልክተው፤ መንግስት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ በመቀበል ወደ ሰላማዊ ህይወት መመለስ ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም የሰላምን አማራጭ እንዲከተሉ የቀረበውን ጥሪ ተከትሎ በርካታ ታጣቂ ሃይሎች እየገቡ መሆኑም ተመልክቷል።
ባለፉት ወራት ያጋጠመውን የጸጥታ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የውይይት መድረኮችን እያካሄዱ መሆኑን የገለጹት ደግሞ ከደቡብ ወሎ ዞን የመጡት የአመራር አባል ወይዘሮ ኮከቤ ሰይድ ናቸው።
የተላለፈው የሰላም ጥሪ ትክክለኛና የሚደገፍ መሆኑንም አስታውቀዋል።
አውቀውም ሆነ ተሳስተው ችግር ውስጥ የገቡ ግለሰቦች የቀረበላቸውን ወርቃማ እድል በመጠቀም ወደ ሰላማዊ አማራጭ በመምጣት በሚካሄዱ የልማት ስራዎች በመሳተፍ ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን መጥቀም እንዳለባቸውም አመልክተዋል።