ቀጥታ፡

በሰለጠንበት ሙያ ሕዝባችንን ለማገልገል ዝግጁ ነን -- የአዲግራት ዩኒቨርሲቲ ተመራቂዎች

አዲግራት ፤ታኅሣሥ 6/2016(ኢዜአ) -- በሰለጠኑበት ሙያ ሕዝባቸውን ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን የአዲግራት ዩኒቨርሲቲ ተመራቂ ተማሪዎች ተናገሩ።

ዩኒቨርሲቲው  ከመጀመሪያ እስከ ሦስተኛ ዲግሪ ባሉት ደረጃዎች  ያሰለጠናቸውን  1ሺህ 839 ተማሪዎች ዛሬ አሰመርቋል።

ተመራቂዎቹ ለኢዜአ እንደተናገሩት በሰለጠኑበት ሙያ  ሕዝባቸውንና አገራቸውን በቅንነት ለማገልገል ተዘጋጅተዋል።

ከተመሪዎቹ መካከል በሦስተኛ ዲግሪ  የተመረቀው ዶክተር ገብረ ሕይወት ወልደ ጊዮርጊስ ''በሰለጠንኩበት ሙያ አገሬን ለማገልገል ቁርጠኛ ነኝ'' ብሏል።


 

በሁለተኛ ዲግሪ የተመረቀው ገብረ ሥላሴ ተስፋይ በበኩሉ በክልሉ ሰላም ሰፍኖ ያቋረጠውን ትምህርት ቀጥሎ ለምረቃ በመብቃቱ ''ደስታዬ ጥልቅ ነው''ሲል ገልጿል።

"በተማርኩበት ሙያ ኅብረተሰቡን ለማገልገል ቁርጠኛ ነኝ'' ያለችው ደግሞ የመጀመሪያ ዲግሪ ሲቪል ምህንድስና ተመራቂዋ  አሰፉ ሃዳስ ናት።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታቸው ረዳ በምረቃው ሥነ ሥርዓት ባስተላለፉት መልዕክት የተማረ የሰው  ኃይል ለልማትና ለዕድገት ወሳኝ መሆኑን ገልጸው የክልሉ መንግሥትም ለትምህርት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

ዩኒቨርሲቲዎች በመሬትና በከርሰ ምድር ውስጥ ያለውን ሀብት ጥቅም ላይ ለማዋልና ሌሎች ችግር ፈቺ ምርምሮችን ማከናወን እንዳለባቸው ያመለከቱት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ብቁ የተማረ የሰው ኃይል በማፍራትም ለኢኮኖሚ ዕድገት አሰተዋፅኦ እንዲያበረክቱም ጥሪ አቅርበዋል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ዛይድ ነጋሽ፣ ዩኒቨርሲቲው 1ሺህ 839 ተማሪዎች ለምረቃ ማብቃቱን ገልጸው፣ ከነዚህም 578ቱ ሴቶች መሆናቸውን ተናግረዋል። 

ከተመራቂዎቹ መካከል 19ኙ በዶክትሬት፣ 34ቱ ደግሞ ሁለተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን ተከታትለው ለምረቃ መብቃታቸውን ተናግረዋል።

አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከ2004 ዓ.ም  ጀምሮ ከ22 ሺህ በላይ በተለያዩ የትምህርት መሰኮች አስመርቆ ለምረቃ ያበቃ ሲሆን፣ የዛሬው ምረቃ ለዘጠነኛ ጊዜ የተካሄደ ነው።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም