አካል ጉዳተኞች በመገናኛ ብዙኃን ትኩረት እንዲያገኙ የሚያስችል መመሪያ እየተዘጋጀ ነው - ኢዜአ አማርኛ
አካል ጉዳተኞች በመገናኛ ብዙኃን ትኩረት እንዲያገኙ የሚያስችል መመሪያ እየተዘጋጀ ነው
አዲስ አበባ ፤ ታህሳስ 6 ቀን 2016 (ኢዜአ)፡-አካል ጉዳተኞች በመገናኛ ብዙኃን ትኩረት እንዲያገኙ የሚያስችል መመሪያ እየተዘጋጀ መሆኑን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ገለጸ።
ባለሥልጣኑ ከኢትዮጵያ ምሁር ዓይነ ስውራን ሴቶች ማኀበር ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የውይይት መድረክ ተካሂዷል።
ውይይቱ መገናኛ ብዙኃን የአካል ጉዳኞች ተጠቃሚነት ጉዳይን አጀንዳ አድርገው እንዲሰሩ ግንዛቤ ለመፍጠር ያለመ መሆኑም ተመላክቷል።
በውይይቱ ላይም የመገናኛ ብዙኃን ሚና፣ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችና መፍትሄዎች ዙሪያ ያተኮረ ጹሁፍ ቀርቦም በተሳታፊዎች ውይይት ተደርጎበታል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ማስተባበሪያ ዳይሬክተር ዱረቲ ታደሰ እንደገለጹት፤ አካል ጉዳተኞች አይችሉም፤ ብቃት የላቸውም የሚለው አሉታዊ አስተሳሰቦችን በማረም ረገድ መገናኛ ብዙኃን ሰፊ ሥራ ይጠበቅባቸዋል።
መሰል አሉታዊ አስተሳሰቦች የአካል ጉዳተኞችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ገድቦት መቆየቱን አስታውሰው በዚህ በኩል የሚስተዋሉ ችግሮችን በመፍታት ሂደት የመገናኛ ብዙኃን ድርሻ የላቀ ሊሆን እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
በኢትዮጵያ ያሉ ዕድሎች፣ አገልግሎቶችና መረጃዎች ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽ እንዲሆኑ ማድረግ ላይ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎችና ተቋማት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ሊወጡ ይገባል ብለዋል።
መገናኛ ብዙኃን ለአካል ጉዳተኞች ጉዳይ ትኩረት እንዲሰጡ ለማድረግ ያለመ የአካል ጉዳተኞች አካቶ ትግበራ መመሪያ እየተዘጋጀ መሆኑን ጠቁመው መመሪያው በተያዘው ዓመት ተጠናቆ ሥራ ላይ እንደሚውል ይጠበቃል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ምሁር ዓይነ ስውራን ሴቶች ማኀበር ሥራ አስኪያጅ በቀለች ጥሩዬ በበኩላቸው የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ ሁነቶችን ጠብቆ ከመዘገብ በዘለለ ቀጣይነት ባለው መልኩ ሽፋን እየተሰጠው አይደለም ይላሉ።
የአየር ሰዓት ይዘው አካል ጉደተኛ ላይ ያጠነጠኑ ፕሮግራሞችን ማዘጋጀት የሚፈልጉ አካል ጉዳተኞችም በመገናኛ ብዙኃን ዘንድ ተቀባይነት እያገኙ አይደለም ያሉት ሥራ አስኪያጇ መሰል ችግሮች ዘላቂ እልባት ይፈልጋሉ ብለዋል።
የአካል ጉዳተኞችን መብትና ጥቅም ለማስከበር የተቋቋሙ ማኀበራትም ከመገናኛ ብዙኃን ጋር ተቀራርበው ሊሰሩ እንደሚገባም አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የንግድ መገናኛ ብዙኃን ክትትልና አቅም ግንባታ ምክትል ዳይሬክተር ሰላማዊት ፈቃደ በበኩላቸው መገናኛ ብዙኃን የአካል ጉዳተኞችን ጉዳይ በተመለከተ ሕግን ተከትለው እየሰሩ ነው ወይ?፣ ምን ዓይነት ክፍተቶች ይታይባቸዋል? በሚሉ ጉዳዮች ላይ ክትትልና ግምገማ እየተደረገ ነው ብለዋል።
በክትትሉ መሰረት ክፍተት የሚስተዋልባቸውን መገናኛ ብዙኃን ማወያየት፣ ማስገንዘብና ከፍ ሲሉም ማሳሰቢያዎች እየተሰጡ መሆኑን አስረድተዋል።