የመከላከያ ዘርፍን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች እየተደረጉ ያሉ ማሻሻያዎች ኢትዮጵያን ለማጽናትና ለማስቀጠል ወሳኝ ናቸው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ - ኢዜአ አማርኛ
የመከላከያ ዘርፍን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች እየተደረጉ ያሉ ማሻሻያዎች ኢትዮጵያን ለማጽናትና ለማስቀጠል ወሳኝ ናቸው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 6/ 2016 (ኢዜአ)፡- የመከላከያ ዘርፍን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች እየተደረጉ ያሉ ማሻሻያዎች ኢትዮጵያን ለማጽናትና ለማስቀጠል ወሳኝ ናቸው ሲሉ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትርና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር )ተናገሩ።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል 88ኛ ዓመት የምስረታ በዓል የማጠቃለያ ሥነ-ሥርዓት ዛሬ በቢሾፍቱ አየር ኃይል ጠቅላይ መምሪያ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
በመርሃ-ግብሩ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትርና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር )፣ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ የመከላከያ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች አየር ኃይል አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ኢብራሒም ናስር፣ ጄኔራል መኮንኖች፣ የአፍሪካ አየር ኃይል አዛዦች የፌደራልና የክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል 88ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል ታላቅ አገር ታላቅ ተቋም የመገንባትና የማጽናት ምልክት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ አየር፣ ምድርና ባህርን ጨምሮ በሁሉም መስኮች ወታደራዊ አቅሟን እየገነባች እንደምትገኝ አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ የመከላከያ ዘርፍን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች እየተደረጉ ያሉ ማሻሻያዎች አገሪቷን ለማጽናትና ለማስቀጠል ወሳኝ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።
ለቀጣዩ ትውልድ ታላቅ አገርና ታላቅ ተቋም ለማስተላለፍ መንግሥት አበክሮ እየሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
ወቅቱን የዋጀ ወታደራዊ ኃይል መገንባት በአዳዲስ ስልቶች የሚመጡ ጥቃቶችን ለመመከት ያስችላል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለዚህም ሁሉም ወገን የበኩሉን ኃላፊነት እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢፌዴሪ አየር ኃይል አቅሙ እንዲገነባ አስተዋጽዖ ላደረጉ አካላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የአየር ኃይሉ 88ኛ ዓመት የምስረታ በዓል "በመስዋዕትነት ሀገርን የዋጀ፤ የኢትዮጵያ አየር ኃይል" በሚል መሪ ኃሳብ ከኅዳር 20 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ሲከበር ቆይቷል።