ኢትዮጵያ ለየትኛውም ኃይል አትበገርም፤ ጥቁር አንበሳ ማሸነፍ እንጂ መሸነፍ አያውቅም- የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ለየትኛውም ኃይል አትበገርም፤ ጥቁር አንበሳ ማሸነፍ እንጂ መሸነፍ አያውቅም- የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 6/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ለየትኛውም ኃይል አትበገርም፤ ጥቁር አንበሳ ማሸነፍ እንጂ መሸነፍ አያውቅም ሲሉ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትርና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል ያሰለጠናቸው አብራሪዎች፣ የበረራ አስተማሪዎች፣ ቴክኒሺያኖችና የነገ የአየር ኃይል መሪ ኦፊሰሮችን አስመርቋል።
በመርሐ ግብሩ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)፣ ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው፣ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ ጀነራል መኮንኖች፣ የክልል ርዕሳነ መሥተዳድሮችና ከንቲባዎች፣ ሚኒስትሮችና የአፍሪካ አየር ኃይል አዛዦች ተገኝተዋል።
የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በ1913 ዓ.ም የመጀመሪያውን አውሮፕላን ወደ ሀገር በመርከብ ስታስገባ ጠንካራ የአስተሳሰብ ተቃውሞ ገጥሞት ተመልሷል።
ሆኖም በ1928 ዓ.ም ጣሊያን ሁለተኛውን ወረራ ስታውጅ ኢትዮጵያ በወቅቱ ያልነበራትን አየር ኃይል በመጠቀም ጥቃት በመክፈቷ ቁጭት ማሳደሩንና አየር ኃይል መቋቋሙን አስታውሰዋል።
ጀግኖች አባቶች የመሠረቱትን አዘምኖ በማስቀጠል ጠንካራ ሀገርና ተቋም መገንባታችንን እንቀጥላለን ብለዋል።
ኢትዮጵያን በሁሉም መስክ ዝግጁ አድርገን እየገነባን የምንገኘውም የነገውን የዓለም ሂደት በማሰብ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል ለታላቋ ኢትዮጵያ ታላቅ ተቋም የመገንባት የፅናት ምልክት መሆኑንም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያን አፅንቶ ለቀጣዩ ትውልድ የማስተላለፍ አደራ የተሸከምን በመሆኑ ያንን ለማሳካት ሌት ተቀን መትጋት የግድ ነው ብለዋል።
የተጀመረውን ለውጥ ለማደናቀፍ ለሚመከሩ ትናንሽ ነገሮች ሳንበገር ወደፊት መገስገስ አማራጭ የሌለው ግዴታችን መሆኑን ማወቅ ይገባል ነው ያሉት።
ጠላት ኢትዮጵያን በተለያየ መልኩ ለማጥቃት እንደሚሞክር በማሰብ ለዚህ የሚመጥንና የመመከት ብቃትና ለጥቃትም አስተማማኝ እርምጃ መውሰድ የሚያስችል ዝግጁነት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
ጠንካራ የተዋጊዎች ስልጠና በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር በመስጠት ህይወት ሰጥተው ጀብዱ በመፈጸም ሀገርን የሚታደጉና የሚያኮሩ የኤሊት ፎርስና የአየር ኃይል ጥምረት እየፈጠረ መሆኑንም ገልጸዋል።
በሁሉም መስክ የተጀመረውን ጥረት በማጠናከር ታላቅ ሀገርና ታላቅ ተቋም በመገንባት ለትውልዱ እናስረክባለን ሲሉም አረጋግጠዋል።
ጥቁር አንበሳ ማሸነፍ እንጂ መሸነፍ አያውቅም ያሉት ጠቅላይ አዛዡ፤ ደፍሮ የሚሞክር ካለ ግብዓተ መሬቱን እናፋጥናለን ነው ያሉት።
አየር ኃይሉን በማዘመን ሂደት ሚናቸውን ለተወጡ ሀገራትም ኢትዮጵያ ውለታ ከፋይ ሀገር ናት እናመሠግናለን ብለዋል።