ኢትዮጵያ ሀገራዊና ቀጣናዊ ተለዋዋጭና ስትራቴጂካዊ ሁኔታዎችን ታሳቢ ያደረገ ጠንካራ መከላከያ ሠራዊት ገንብታለች-ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ሀገራዊና ቀጣናዊ ተለዋዋጭና ስትራቴጂካዊ ሁኔታዎችን ታሳቢ ያደረገ ጠንካራ መከላከያ ሠራዊት ገንብታለች-ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 6/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ሀገራዊና ቀጣናዊ ተለዋዋጭና ስትራቴጂካዊ ሁኔታዎችን ታሳቢ ያደረገ ጠንካራ መከላከያ ሠራዊት መገንባቷን የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል ያሰለጠናቸው አብራሪዎች፣ የበረራ አስተማሪዎች፣ ቴክኒሺያኖችና የነገ የአየር ኃይል መሪ ኦፊሰሮችን አስመርቋል።
በመርሐ ግብሩ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)፣ ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው፣ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ ጀነራል መኮንኖች፣ የክልል ርዕሳነ መሥተዳድሮችና ከንቲባዎች፣ ሚኒስትሮችና የአፍሪካ አየር ኃይል አዛዦች ተገኝተዋል።
የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በዚህ ወቅት ባደረጉት ንግግር፣ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የምድር ኃይል፣ አየር ኃይል፣ ባህር ኃይልና ሌሎች ጦር ክፍሎችን መገንባቷን ተናግረዋል።
የቀጣናው ተለዋዋጭና ስትራቴጂክ ሁናቴ የዓለም የኃይል አሰላለፍና የዘመኑ የውጊያ አውድ ኢትዮጵያ ሁሉንም የመከላከያ ኃይሎችን እንድታዘምን የሚያስገድድ መሆኑን አንስተዋል።
ከጦር ኃይሎች መካከል የኢትዮጵያ አየር ኃይል ተልዕኮውን በብቃት መፈጸም የሚያስችል አቅም እንዲፈጥር በሚያደርግ መልኩ መዘመኑን ገልጸዋል።
በዚህም በኢትዮጵያ ላይ ሊቃጣ የሚችልን ጦርነት በሩቁ የሚያስቀር አየር ኃይል ሆኗል ብለዋል።