ቀጥታ፡

በአሁኑ ወቅት  የሚስተዋለው  ቅዝቃዜ ለመስኖ ልማት በተዘጋጁ ችግኞች ላይ  ጉዳት  እንዳያስከትል ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል

ሐረር ፤ ታህሳስ 6 /2016 (ኢዜአ)፡-  በአሁኑ ወቅት እየተስተዋለ ያለው ቀዝቃዛማ የአየር ሁኔታ ለመስኖ ልማት በተዘጋጁ ችግኞች ላይ  ጉዳት  እንዳያስከትል አርሶ አደሩ  ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ ተመለከተ።

የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ይፋ ባደረገው የትንበያ መረጃ መሰረት  ከደረቃማ የእርጥበት ሁኔታ ጋር ተያይዞ በሰሜን፣ በምስራቅና በደቡብ ደጋማ ሥፍራዎች ላይ የሌሊቱና የማለዳው ቅዝቃዜ ቀጣይነት እንደሚኖረው ተመልክቷል። 


 

በዚህም  በተለይም እድገታቸውን ላልጨረሱ፣ ፍሬ በመሙላት ላይ የሚገኙ ሰብሎችና ቋሚ ተክሎች ላይ ጉዳት ሊያስከትል  ስለሚችል አርሶ አደሮችና የሚመለከታቸው አካላት የሚኖረውን ቅዝቃዜ ለማሻሻል የሚረዱ ተግባራትን ማከናወን እንዳለባቸው ነው የተጠቆመው።

ይህን ተከትሎ ኢዜአ ያነጋገራቸው  የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የዘርፉ  ምሁራን እንዳሉት፤ በአሁኑ ወቅት እየስተዋለ ያለው ቀዝቃዛማ የአየር ሁኔታ ለመስኖ ልማት  በተዘጋጁ ችግኞች ላይ  አሉታዊ ተጽዕኖ ይኖረዋል።

ችግሩን ለመቋቋም አርሶ አደሩ ችግኞችን በዳስ በመከለልና አቅም በፈቀደ አረንጓዴ ቤት በመስራት መጠቀም እንዳለበት አመላክተዋል። 

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የአግሮ ሜትሮሎጂ መምህርና የክላይሜት ስማርት የሶስተኛ ዲግሪ ተማሪ ዕጩ ዶክተር አብዲሳ አለሙ እንደገለጹት፤  በኢትዮዽያ ህዳር፣ታህሳስና ጥር ቀዝቃዛማ የአየር ጸባይ ያላቸው ወራቶች ናቸው።

በተለይ በምስራቅና መካከለኛው ኢትዮጵያ ላይ እስከ ጥር አጋማሽ ድረስ በጠዋትና በሌሊቱ ወቅቶች  ከፍተኛ ቅዝቃዜ እንደሚያይል አስረድተዋል።

በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ  በመኸር ወቅት የለማው ሰብል በአብዛኛው እንደተሰበሰበ መገመት እንደሚቻል ያመለከቱት ምሁሩ፤ አሁን የሚስተዋለው  ቀዝቃዛማው የአየር ሁኔታ በተለይ ለመስኖ ዝግጅት እየተከናወነ በሚገኘው ችግኝ ላይ ጉዳት ሊስከትል እንደሚቻል ተናግረዋል።

በዚህም አርሶ አደሩ በመስኖ ለማልማት እያዘጋጀ የሚገኘው የአትክልት ችግኞች በቀዝቃዛ አየር ንብረት እንዳይጎዳ ዳስ በማዘጋጀት አልያም አቅም በፈቀደ  የአረንጓዴ ቤት በመስራት መከላከል እንደሚችል ጠቁመዋል።

በግብርናው ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶች ግን ምርቶቻቸው በአየር ንብረቱ ከጥቅም ውጪ እንዳይሆን የአረንጓዴ ቤት በመስራት  መከላከል እንደሚቻልም ገልጸዋል።

በተጨማሪም አርሶ አደሩ ከተራራ ላይ የሚነፍሰው ቀዝቃዛ አየር ችግኞችን ስለሚጎዳ ሌላ አካባቢ  ችግኝ የማፍላት ስራ ቢያከናውን እንደሚመረጥ  ምክር ለግሰዋል።


 

ሌላው የዩኒቨርሲው የአግሮሜትሮሎጂ መምህር ግርማ አሰፋ በበኩላቸው፤ በአሁኑ ወቅት የሚስተዋለው  የቅዝቃዜና ውርጭ ክስተት እድገታቸውን ላልጨረሱ የመስኖ ሰብሎችና ችግኞች ላይ ጉዳት እንዳያደርስ መጠንቀቅ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

ይህም  አርሶአደሩ ጠዋት  ላይ በማሳ ውስጥ ሳርና ሌሎች የደረቁ ቅጠሎችን እያቃጠለ በማጨስ ሙቀት የማምጣት ስራዎችን ማከናወን አለበት  ብለዋል።

ለአትክልት ችግኞች ግን አረንጓዴ ቤት /ሼድ/በመስራት ከቀዝቃዛው አየር ጉዳት ችግኞችን መታደግ እንደሚቻል  አመልክተዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም