ቀጥታ፡

ጥቁር አንበሳ የአየር ትርዒት ብቃት ያለው አብራሪ በመሆን አገርን ለማገልገል ተነሳሽነት ፈጥሮብናል - የአየር ኃይል አካዳሚ የበረራ ሠልጣኞች

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 6/2016(ኢዜአ)፦ ጥቁር አንበሳ የአየር ትርዒት ሙያዊ ብቃት በማዳበር የኢትዮጵያን አየር ክልል ለመጠበቅ ላላቸው ዓላማ ስንቅ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ አየር ኃይል አካዳሚ የበረራ ሠልጣኝ ተማሪዎች ገለጹ።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል 88ኛ ዓመት የምስረታ በዓል የማጠቃለያ ሥነ-ሥርዓት ዛሬ በቢሾፍቱ አየር ኃይል ጠቅላይ መምሪያ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

በመርኃ-ግብሩ “ጥቁር አንበሳ" የተሰኘ የአየር ትርዒት የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች አየር ኃይል አባላት ከኢትዮጵያ አየር ኃይል ጋር በመሆን አከናውነዋል።


 

ኢዜአ የአየር ትርዒቱን በሥፍራው ተገኝተው የተከታተሉ የኢትዮጵያ አየር ኃይል አካዳሚ የበረራ ሠልጣኝ ተማሪዎችን አነጋግሯል።

ሠልጣኞቹም የአየር ትርዒቱ የአየር ኃይል አብራሪነት የሚፈልገውን የሙያ ብቃት በማጎልበት አገራቸውን በከፍተኛ ሙያዊ ኃላፊነት ለማገልገል መነሳሳት እንደፈጠረባቸው ገልጸዋል።  

በአካዳሚው የሁለተኛ ዓመት የበረራ ተማሪ የሆነችው ካዴት መርሰን ግርማ፤ ትርዒቱ ልብን የሚያሞቅና ደስ የሚያሰኝ ስሜት እንደፈጠረባት ገልጻለች።

ትርዒቱ ተግቶና ጠንክሮ በመሥራት አገርን ማገልገል እንደሚቻል ትምህርት ወስጄበታለሁ ብላለች።

በኢትዮጵያ የሴት አየር ኃይል አብራሪዎች በብዛት እንደማይገኙ ገልጻ ትምህርቷን አጠናቃ አብራሪ በመሆን ለሌሎች እንስቶች አርዓያ መሆን እንደምትፈልግ ተናግራለች።

የአንደኛ ዓመት የበረራ ተማሪ የሆነው ካዴት ጫላ ጉቱ በበኩሉ፤ በትርዒቱ የተመለከተው ነገር አገሩን ለማገልገል ይበልጥ ተነሳሽነት እንደፈጠረበት ገልጿል።

የአየር ኃይል አባል በመሆኑ ኩራት እንደሚሰማው ገልፆ፤ ወደፊት የአየር ኃይል አብራሪ ለመሆን ሕልሙን ለማሳካት በትጋት እንደሚሰራ ተናግሯል።

ሌላኛዋ የበረራ ተማሪ ካዴት ሐና ግርማ፤ በትርዒቱ አንድ ሰው ዓላማውን ለማሳካት ከተጋ ጥሩ ደረጃ ላይ መድረስና ስኬታማ መሆን እንደሚችል የተማርኩበት ነው ብላለች።

ሌላኛው የኢትዮጵያ አየር ኃይል አካዳሚ የበረራ ተማሪ የሆነው ካዴት በፍቃዱ ዓለማየሁ፤ ወታደር መሆን የዓላማ ጽናትና አገርን መውደድ አጣምሮ የሚሰጥ ሙያ መሆኑን ገልፆ፤ ወታደርም አብራሪም መሆን ልዩ ስሜት እንደሚፈጥር ተናግሯል።

ትምህርቱን ጠንክሮ በመማር አገሩን ለማገልገል ዝግጁ ነኝ ብሏል።

 ሠልጣኝ ተማሪዎቹ የአየር ኃይል አብራሪ በመሆን የሚወዷትን ኢትዮጵያን በማገልገል ትልቅ ታሪክ ለመሥራት እንደሚፈልጉ ገልፀዋል። 

የአየር ኃይሉ 88ኛ ዓመት የምስረታ በዓል "በመስዋዕትነት ሀገርን የዋጀ፤ የኢትዮጵያ አየር ኃይል" በሚል መሪ ኃሳብ ከኅዳር 20 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ እየተከበረ ይገኛል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም