ጥቁር አንበሳ የአየር ትርኢት ኢትዮጵያና የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች በጋራ ለመሥራት ያላቸውን ጽኑ ፍላጎት በግልጽ ያሳየ ነው - ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ - ኢዜአ አማርኛ
ጥቁር አንበሳ የአየር ትርኢት ኢትዮጵያና የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች በጋራ ለመሥራት ያላቸውን ጽኑ ፍላጎት በግልጽ ያሳየ ነው - ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 6/2016(ኢዜአ)፦ጥቁር አንበሳ የአየር ትርኢት ኢትዮጵያና የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች በሁለትዮሽና ቀጣናዊ ጉዳዮች በጋራ ለመሥራት ያላቸውን ጽኑ ፍላጎትና ትብብር በግልጽ ያሳየ መሆኑን የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ገለጹ።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል 88ኛ ዓመት የምስረታ በዓል የማጠቃለያ ሥነ-ሥርዓት በቢሾፍቱ ከተማ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
በሥነ-ሥርዓቱ የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች አየር ኃይል አባላት ከኢትዮጵያ አየር ኃይል ጋር በመሆን “የጥቁር አንበሳ የአየር ትርዒት” አሳይተዋል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ የአየር ትርኢቱን አስመልክተው ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸው ኢትዮጵያና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በፖለቲካውም በውትድርናውም መስክ መልካም ግንኙነት ያላቸው ወዳጅ አገራት መሆናቸውን አንስተዋል።
በዚህም የጋራ አቅምን አስተባብሮ በመጠቀምና ልምድ በመለዋወጥ ረገድ ውጤታማ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
ዛሬ በሁለቱ አገራት አየር ኃይሎች ስኬታማ የአየር ትርኢት ማሳየት መቻሉ የትብብር ሥራው ማሳያ ነው ብለዋል።
በስኬት የተከናወነውን “የጥቁር አንበሳ የአየር ትርዒት” በማስፋት በዓለም ከታወቁ የአየር ትርኢቶች ተርታ ለማሰለፍ እንደሚሰራም ተናግረዋል።
ለዚህም በርካታ አገራት ፍላጎት ያላቸው መሆኑን በመጥቀስ ሰሞኑን በተካሄደው የአፍሪካ አየር ኃይል አዛዦች ፎረም ላይ ለዚህ አጋዥ የሆኑ ሥምምነቶች መደረጋቸውን ጠቁመዋል።
በፎረሙ የአፍሪካ አገራት ለመተጋገዝና መሰረተ ልማቶችን በጋራ ለመጠቀም በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ መግለጻቸውን አንስተዋል።
ከዚህም ባሻገር የኢትዮጵያ አየር ኃይል አካዳሚ አቅም የማሳደግ ሥራ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
የተለያዩ አፍሪካ አገራት የሥልጠና ፍላጎት ያላቸው በመሆኑ ይህንን ታሳቢ ያደረጉ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል 88ኛ ዓመት የምስረታ በዓል "በመስዋዕትነት አገርን የዋጀ የኢትዮጵያ አየር ኃይል" በሚል መሪ ኃሳብ ከሕዳር 20 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ እየተከበረ ይገኛል።