የትምህርት ዘርፉን ከገጠመው ችግር ለማውጣት የግብዓት፣ የመምህራን አቅምና የተማሪዎች ሥነ ምግባር ትኩረት ሊደረግበት ይገባል --ባለድርሻ አካላት - ኢዜአ አማርኛ
የትምህርት ዘርፉን ከገጠመው ችግር ለማውጣት የግብዓት፣ የመምህራን አቅምና የተማሪዎች ሥነ ምግባር ትኩረት ሊደረግበት ይገባል --ባለድርሻ አካላት
ዲላ ፤ ታህሳስ 6/2016 (ኢዜአ)፡- የትምህርት ዘርፉን ከገጠመው ችግር ለማውጣት የመምህራን አቅምና የተማሪዎች ሥነ ምግባር ትኩረት ሊደረግበት እንደሚገባ ባለድርሻ አካላት ገለጹ።
ከትምህርት ባለድርሻ አካላቱ መካከል የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ምክትል ፕሬዚዳንት መምህር ሽመልስ አበበ ማህበሩ የመምህራን ሥልጠና ጥራት በማሻሻል ጥራት ያለው ትምህርት ለመስጠት አግባብ ካላቸው አካላት ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
የመምህራን አቅም ውስንነት ለትምህርት ጥራት መጓደል ቀዳሚውን ድርሻ እንደሚይዝ የተናገሩት መምህር ሽመልስ፣ይህም ከምዘና ሥርዓትና ከተማሪዎች ሥነ ምግባር ብልሽት ጋር ተዳምሮ የትምህርት ሥርዓቱን ችግር ውስጥ ከትቶታል ብለዋል፡፡
የመምህርነት ሙያና የከፍተኛ ትምህርትና ሥልጠና ተለያይተው መሰጠታቸው እንዲሁም የመምህራን ምልመላ መስተካከል እንደሚገባው ምክትል ፕሬዚዳንቱ ጠቁመዋል።
''የከፍተኛ ትምህርት ዕውቀት ያለው ሁሉ መምህር ሊሆን አይችልም''ያሉት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፣ መምህር ከሳይንሳዊ ዕውቀት በተጨማሪ የዳበረ የማስተማር ሥነ ዘዴ ክህሎት ሊኖረው ይገባዋል ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ማህበሩ መምህራን በየጊዜው ዕውቀታቸውንና ክህሎታቸውን እንዲያሻሽሉ ከመሥራት በተጓዳኝ የመምህራን ሥልጠና ጥራትን ለማሻሻል ከመንግሥት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሐብት ልማት ሥራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የትምህርት ዘርፍ አስተባባሪ ዶክተር ማስተዋል መኮንን በትምህርት ሥርዓት ውስጥ የሚስተዋሉ የግብዓት፣ የመምህራን አቅምና የተማሪዎች ሥነ ምግባር ችግሮች መስተካከል ይገባቸዋል ብለዋል።
በተለይም መንግሥት፣ ምሁራንና የትምህርት ተቋማት የትምህርት ጥራት ችግሮችን የጋራ መፍትሄ ማፈላለግ ይገባቸዋል በማለትም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ቋሚ ኮሚቴው የትምህርት ጥራት ችግርን ለማቃለል በተለይ በምዘና ጎልተው የወጡ ተግዳሮቶችን ለማስተካከል እያገዙ መሆኑን አስተባባሪዋ ተናግረዋል።
የሲዳማ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደርና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ በየነ በራሶ በበኩላቸው በክልሉ በትምህርት ሥርዓቱ ሥር ነቀል ለውጥ ለማምጣት ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል።
ከነዚህም በዋነኝነት "ትምህርት ለትውልድ ንቅናቄና የሲዳማ የትምህርት ተሃድሶ" ፕሮግራም ተነድፎ በመምህራን ልማት፣ በቅድመ አንደኛ ትምህርት ቤት ግንባታ፣ በግብዓትና መሰል ዘርፎች ላይ እንደተተኮረ በማመላከት።
በዚህም በታችኛው የትምህርት እርከን በተማሪዎች የንባብ ክህሎት ላይ መሻሻል መታየቱን ያስረዱት አቶ በየነ፣ በክልሉ መንግሥት በተመደበ 346 ሚሊዮን ብር ወጪና በፌደራል መንግሥት ድጋፍ የአዲሱ የትምህርት ሥርዓት የተማሪዎች የመማሪያ መጻህፍት ለሁሉም የትምህርት ደረጃዎች እንዲደርስ መደረጉን ተናግረዋል።
የጌዴኦ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ዘማች ክፍሌ፣ በዞኑ አዲሱ የትምህርት ሥርዓት በሙሉ አቅም ወደ ሥራ መግባቱን ተናግረው ለዚህም ትምህርት ቤቶችን ለመማር ማስተማር ሥራ ምቹ የማድረግ፣ የመምህራን ብቃት ማሻሻልና ማህበረሰቡን ያሳተፈ የግብዓት አቅርቦት እየተከናወነ ነው ብለዋል።
የዲላ ዩኒቨርሲቲ "የኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት ቀውስ ተግዳሮት፣ ዕድልና የመፍትሄ አቅጣጫ" በሚል መሪ ሐሳብ 11ኛው ሀገር አቀፍ የትምህርት ዐውደ ጥናትን ማስተናገዱ ይታወሳል።