የኮይሻ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ ለሃገር ያለው ፋይዳ የጎላ ነው - ቋሚ ኮሚቴው - ኢዜአ አማርኛ
የኮይሻ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ ለሃገር ያለው ፋይዳ የጎላ ነው - ቋሚ ኮሚቴው
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 6/2016(ኢዜአ)፦ የኮይሻ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ ኢትዮጵያን ወደ ፊት ሊያራምድ የሚችልና በዓለም ደረጃ ተወዳዳሪ እንደሚያደርጋት የመንግስት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ።
ቋሚ ኮሚቴው የኮይሻ ኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጫ የፕሮጀክት ግንባታ አፈፃፀምን ተመልክቷል።
የኤሌክትሪክ ሀይል የልማቶች ሁሉ የጀርባ አጥንት በመሆኑ የሀገሪቱ አቅም በፈቀደ መጠን ጉድለቶች እንዲስተካካሉ የክትትልና የቁጥጥር ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተገልጿል።
የቋሚ ኮሚቴው ቡድን አስተባባሪ አቶ እያሱ ዛላ ፕሮጀክቱ ድልድይ፣ መንገድ እና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን በመስራት የአካባቢው ማህበረሰብ እርስ በዕርሱ እንዲገናኝ የሰራውን ሥራ አድንቀዋል።
ለስራው መፍጠን የተለያዩ የግብዓት አቅርቦቶች መሟላት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የሚፈጠሩ የፀጥታ ችግሮች በሚፈጥሩት አለመረጋጋት አንዳንድ ፕሮጀክቶች ችግር እያጋጠማቸው እንደሆነ አንስተው፤ በፕሮጀክቱ ላይ ጫና የሚያሳድሩ በመሆኑ ያለውን አቅም አሟጦ መጠቀም ይገባል ብለዋል።
ፕሮጀክቱ ለአገር ከሚሰጠው ፋይዳ አንፃር የሚመለከተው አካል በሙሉ ተረባርቦ መስራት እንዳለበት አስገንዝበዋል።
ቋሚ ኮሚቴውም ማነቆዎች እንዲፈቱ ለሚመለከተው አካል ያሳውቃል ብለዋል።
የኮይሻ ፕሮጀክት የኮንትራት አስተዳዳሪ ኢንጅነር እዮኤል ሰለሞን ፕሮጀክቱን የሚያስተዳድረው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል እንደሆነ ጠቁመው፣ ፕሮጀክቱ የፋይናንስ ማነቆ እንዳጋጠመውና አሁን ላይ አጠቃላይ አፈፃፀሙ 62 በመቶ መሆኑን ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱ መጠናቀቅ ከነበረበት 1 ዓመት እንዳለፈና የስራ ተቋራጩ የቀሩ ስራዎችን እንዲጨርስ እየተወያየን ነው ብለዋል።
ፕሮጀክቱ በፋይናንስ እጥረት ሳቢያ እንዳይዘገይ ተገቢው መፍትሄ ሊሰጠው እንደሚገባም መግለጻቸውን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መረጃ ያመለክታል።