ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ልዑካን ከ3 የብሪታንያ የንግድ ምክር ቤቶች ጋር የልምድ ልውውጥ አካሔዱ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 6/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የልዑካን ቡድን በለንደን ከተማ ከሚገኙ 3 የብሪታንያ የንግድ ምክር ቤቶች ጋር የልምድ ልውውጥና የትብብር ግንኙነት ውይይት አደረጉ፡፡

የልምድ ልውውጥ መርሃ-ግብሩ የተካሔደው በለንደን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ኤምባሲ አስተባባሪነት ከዩናይትድ ኪንግደም ከሚገኙ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ጋር በመቀናጀት እ.ኤ.አ ከዲሴምበር 13-15/2023 ባዘጋጀው ፕሮግራም ነው።

ሶስቱ የንግድ ምክር ቤቶች የብሪቲሽ ንግድ ምክር ቤት፤ የብሪቲሽ-ኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤትና የለንደን ንግድ ምክር ቤት ናቸው።

በሶስቱም መድረኮች የለንደን ኤምባሲ ምክትል ሚስዮን መሪ አቶ በየነ ገብረ መስቀል በአስተባባሪነትና ተወያይነት የተሳተፉ ሲሆን ከኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ደግሞ ፕሬዜዳንቱ መላኩ እዘዘው(ኢንጅነር) እና የምክር ቤቱ ጸሃፊ አቶ ውቤ መንግስቱ ከሌሎች 9 የቦርድ አባላት ጋር ተሳትፈዋል።


 

ኢትዮጵያ ስላላት የኢንቨስትመንትና የንግድ እድሎች ማስረዳት ከመቻሉም በላይ ይህንን እድል ለመጠቀም በሚቻልበት አግባብ ላይ ከንግድ ምክር ቤቶቹ ጋር ምክከር ተደርጓል።

የብሪቲሽ የንግድ ዘርፍ ምክር ቤት ዳይሬክተር አን ሜሪ ማርቲን ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት፣ ለቱሪዝምና ለንግድ ሥራዎች እምቅ አቅም ያላት አገር መሆኗን እንደተገነዘቡ ገልጸው በዩናይት ኪንግደም የሚገኙ ሌሎች የንግድ ምክር ቤቶችን በማስተባበር በቀጣይ ትስስር ለመፍጠር የማመቻቸት ሥራ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

የብሪቲሽ–ኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ሰብሳቢ ዶክተር አርቲ ኃይሰኒ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ያሉ የኢንቨስትመንት፣ የቱሪዝምና የንግድ እምቅ አቅሞችን ለይተው እንደሚያውቋቸው ልምዳቸውን አካፍለዋል።

አስከትለውም በሃገሪቱ በርካታ ለውጦች እንዳሉ ሆነው አንዳንድ ወሳኝ የሚታዩ የኢንቨስትመንትና የንግድ ማነቆዎችን በጋራ ተቀናጅቶ መፍታት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የለንደን የንግድ ምክር ቤት የዓለም አቀፍ ፓርትነርሺፕ ኃላፊ ማርታ ኮዝሎውሳካ የንግድ ምክር ቤታቸው በኢትዮጵያ የሚገኙ የንግድ አጋሮችና በዩናይት ኪንግደም ከሚገኙ የንግድ አጋሮች ጋር ተቀናጅተው መሥራት እንዲችሉ በንግድ ምክር ቤታቸው በኩል የበኩላቸውን እገዛ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያና የዩናይትኪንግደም የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤቶች ተቋማዊ የትብብር ማእቀፍ በማዘጋጀት በቀጣይ አብሮ ለመስራት የሚቻልባቸውን ሁኔታዎች ማመቻቸት እንዳለባቸው፣ የልምድ ልውውጥ ፕሮግራሙም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት መግባባት ላይ ተደርሷል።

በዩናይት ኪንግደም የንግድ ምክር ቤቶች በኩል ለኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት የአቅም ግንባታ ድጋፍ ለማድረግና ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮችን በቀጣይ ውይይቶችና ግኑኝነቶች ለመፈጸም መታቀዱ ተገልጿል።

በማጠቃለያውም የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት አባላት በተገኙበት በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጉብኝት ከተካሔደ በኋላ ለዩኬ-አፍሪካ ኢንቨስትመንት ሰሚት ከወዲሁ መደረግ ስላለባቸው ዝግጅቶች ምክክር ተደርጓል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም