ቀጥታ፡

የስኳር ፋብሪካዎችን የማምረት አቅም ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው

አዳማ ፣ታህሳስ 05/2016 (ኢዜአ)፦ የስኳር ፋብሪካዎችን የማምረት አቅም ለማሳደግ የአገዳ ልማትና የግብዓት አቅርቦት ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አብዱረህማን ኢድ ገለፁ።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ የቦርድ አመራሮች የወንጂ ስኳር ፋብሪካ የምርት እንቅስቃሴና በፋብሪካው እየተከናወኑ ያሉ የሌማት ቱሩፋት እንዲሁም የፐልፕና ወረቀት ፋብሪካን ጎብኝተዋል።

የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አብዱረሃማን ኢድ እንደገለፁት የስኳር ፋብሪካዎችን የማምረት አቅም ለማሳደግ እየተሰራ  ነው።

በተለይም የወንጂ፣ ኦሞ ሁለትና ሶስት እንዲሁም ጣና በለስ፣ ከሰምን ጨምሮ የስኳር ፋብሪካዎች ያለባቸውን የአቅርቦት ችግር የመፍታት ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው የአገዳ፣ የመለዋወጫ እቃዎች አቅርቦትና ሌሎች ተያያዥ ችግሮችን የመፍታት ስራ እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።

ዛሬ የተደረገው ጉብኝትም የወንጂ ስኳር ፋብሪካ የዘንድሮውን የማምረት ስራ ማስጀመርና ቀጣይ የዝግጅት ሁኔታውን መመልከት ነው ብለዋል።

በዚህም ፋብሪካው ከአገዳ ልማትና አቅርቦት፣ ከመለዋወጫ መሳሪያዎች አንፃር ዝግጅቱን አጠናቆ ወደ ምርት መግባቱን የገለፁት ዋና ስራ አስፈፃሚው የማምረት አቅሙን በዓመት 1 ሚሊዮን ኩንታል ለማድረስ በትኩረት እንደሚሰራም ገልጸዋል።

የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዘዳንትና የቦርድ አመራሩ አባል አቶ አወሉ አብዲ በበኩላቸው የሸንኮራ አገዳ ልማት ስራ ፋብሪካውና የአካባቢው አርሶ አደሮች በጋራ እንዲያለሙ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በተለይ የውሃ እጥረት ለመቅረፍ ከፍተኛ ጉልበት ያላቸው ጄነሬተሮች ተገዝተው እየገቡ መሆኑን ጠቅሰው የአገዳ ምርት ለማሳደግ ከአርሶ አደሩ ጋር ውይይት በማድረግ ወደ አገዳ ልማት እንዲገቡ  ተደርጓል ብለዋል።

በዚህም በፋብሪካው የሚለማውን የሸንኮራ አገዳ ማሳ ልማት ወደ 9ሺህ ሄክታር ማድረስ መቻሉን አመልክተው በቀጣይ የአገዳ ማሳውን ወደ 14 ሺህ ሄክታር ለማሳደግ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

በተጨማሪም በፋብሪካው ውስጥ በሌማት ቱሩፋት መርሃ ግብር የዶሮ፣ የእንስሳት ማድለብ፣ የንብ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ልማት እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ዋዮ ሮባ በበኩላቸው ፋብሪካውዎቹ ያለባቸው የአገዳ ምርትና የመለዋወጫ ዕቃዎች ውስንነት በራሳቸው አቅም ጭምር እንዲፈቱ የማስተሳሰር ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ አንስተዋል።

በዚህም የስኳር ምርት ከማሳደግ ባለፈ የአገዳ አምራች  አርሶ አደሮችን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ረገድ ሚናው የጎላ መሆኑንም ገልጠዋል።

በአሁኑ ወቅት የአብዛኛው ፋብሪካዎች የማምረት አቅም እስከ 350 ሺህ ኩንታል መሆኑን የገለፁት አቶ ዋዮ በቀጣዩ ዓመት የወንጂ ፋብሪካን የማምረት አቅም  ከ1 ሚሊዮን ኩንታል በላይ  ለማድረስ ግብ ተቀምጦ እየተሰራ ነው ብለዋል።

የወንጂ ስኳር ፋብሪካ ከአገዳና ተያያዥ የግብዓት አቅርቦት እጥረት ጋር ተያይዞ 30 በመቶ ብቻ እያመረተ ሲሆን በአሁኑ ወቅት የነበሩትን ችግሮች በመቅረፍ የተሻለ ለማምረት የሚያስችል አቅምና ዝግጅት ማድረጉንም አመልክተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም