ቀጥታ፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በጥናትና ምርምር የተደገፈ ፍትሃዊ  የንግድ ሥርዓት ለማስፈን የሚያስችል ስምምነት ተፈራረመ

አዲስ አበባ ፤ታህሳስ 5/2016 (ኢዜአ)፦ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በጥናትና ምርምር የተደገፈ ፍትሃዊ የንግድ ሥርዓት ለማስፈን የሚያስችል ስምምነት ከኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ጋር  ተፈራረመ።

ስምምነቱን  የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ገብረመስቀል ጫላ እና የኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ተፈራርመዋል።

ሚኒስትሩ ገብረመስቀል ጫላ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ እንደ ሀገር ፍትሃዊ የንግድ ሥርዓት ለመገንባት ዘመናዊ የንግድ አሠራር መዘርጋት ያስፈልጋል።


ተቋሙ ከዚህ በፊት ተወዳዳሪ የንግድ ሥርዓት ለመፍጠር ባከናወናቸው ተግባራት  አበረታች ለውጦች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።

ነገር ግን አልፎ አልፎ በፍትሃዊነትና በሸማቾች መብት ጥበቃ ዙሪያ መፍትሔ የሚሹ ተግዳሮቶች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

እነዚህን ተግዳሮቶች በዘላቂነት ለመፍታት የምርምር ተቋማት እገዛ እንደሚያስፈልግ የጠቀሱት ሚኒስትሩ፤ የዛሬው ስምምነትም ይህን ታሳቢ ያደረገ ነው ብለዋል።

ጥናትና ምርምሮችን ማድረግ፣ አዳዲስ ሃሳቦችን ማመንጨትና ማማከር የስምምነቱ  መስኮች መሆናቸውን ተናግረዋል።

በቀጣይም ይህንና መሰል ተግባራትን በማከናወን በጥናትና ምርምር የተደገፈ ፍትሃዊ  የንግድ ሥርዓት ለማረጋገጥ በትኩረት  እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በበኩላቸው፤ የመንግሥትን ሥራ ለሚያከናውኑ መሥሪያ ቤቶች በምርምር የተደገፈ መረጃ ማቅረብ የኢንስቲትዩቱ ዐብይ ተግባር  ነው ብለዋል።

ተቋሙ ከዚህ በፊት ትክክለኛና ፍትሃዊ መረጃዎችን በማቅረብ ለተለያዩ መሥሪያ ቤቶች እገዛ ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል።

በቀጣይም የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የግብይት ሥርዓትን ለማዘመን በሚያደርገው ጥረት በምርምር የተደገፈ መረጃ በመስጠት በትብብር የሚሰራ ይሆናል ብለዋል።
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም