የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በአየር ኃይል የተሰሩ ፕሮጀክቶችን መረቁ - ኢዜአ አማርኛ
የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በአየር ኃይል የተሰሩ ፕሮጀክቶችን መረቁ
አዲስ አበባ ፤ ታህሳስ 5/2016 (ኢዜአ)፦ የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በአየር ኃይል የተሰሩ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን መርቀው ከፈቱ።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከአገልግሎት ውጪ የነበሩ ትጥቆችን በማዘመን የዝግጁነት አቅሙን ማሳደግ እንደተቻለም ተገልጿል።
ከተመረቁ ፕሮጀክቶች መካከል በአየር ኃይል ከባድ ጥገና ማዕከል አማካኝነት ከአገልግሎት ውጭ የነበሩ አውሮፕላኖችን በመጠገን ወደ ዝግጁነት መመለስ የተቻለበት ስራ ይጠቀሳል።
በተጨማሪም አየር ኃይሉ በራሱ አቅም ያስገነባው የእግር ኳስ ስታዲየምና ሌሎች ፕሮጀክቶች ተመርቀዋል።
የተመረቁ ፕሮጀክቶችን ጨምሮ በአየር ኃይሉ ቅጥር ግቢ የተከናወኑ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት፣ የግቢ ማስዋብና በቴክኖሎጂ ፈጠራ የታገዘ የትጥቅ አቅም ማሻሻያ ስራዎች በሠራዊቱ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች፣ በመንግስት የስራ ኃላፊዎችና ተጋባዥ እንግዶች ተጎብኝተዋል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል ለትራንስፖርት አገልግሎት ሲውሉ የነበሩ ሄሊኮፍተሮችን ወደ ተዋጊነት በማሳደግ፤ ከአገልግሎት ውጭ የነበሩ አውሮፕላኖችን በራስ አቅም በመጠገን ወደ ዝግጁነት መመለስ የሚያስችሉ ውጤታማ ስራዎች ማከናወኑም በጉብኝቱ ተገልጿል።