ኢትዮ-ቴሌኮም አራት ዘመናዊ አገልግሎቶችን አስጀመረ

አዲስ አበባ ፤ ታህሳስ 5/2016 (ኢዜአ)፦ ኢትዮ-ቴሌኮም የዓለም አቀፍ የቴሌኮም ኢንዱስትሪ መስፈርትን ያሟሉ አራት አዳዲስ አገልግሎቶችን ዛሬ በይፋ አስጀምሯል።

ኩባንያው ያስጀመራቸው የቮልቲኢ፣ የሪች ኮሙኒኬሽን፣ የመልቲ ሚዲያና የድምፅ መልዕክት አገልግሎቶች እንደሆኑ ነው የተገለፀው።

ቮልቲኢ አገልግሎት፤ ዓለም አቀፍ የቴሌኮም ኢንዱስትሪ መስፈርትን ያሟላ ከመደበኛው የላቀ የድምፅና የምስል ጥራት ያለው አገልግሎት ለደንበኞች ማድረስ የሚያስችል መሆኑም ተጠቁሟል።

የሪች ቢዝነስ መልዕክት አገልግሎት፤ የግለሰብና የንግድ ደንበኞች የመደበኛ መልዕክት አገልግሎትን ተጠቅመው ከጽሑፍ መልዕክት ባሻገር ፎቶ ወይም ቪዲዮን ጨምሮ የተለያዩ መረጃዎችን በኢንተርኔት አገልግሎት ማጋራት የሚያስችል ዘመናዊ መሳሪያ መሆኑ ተነግሯል።


 

የመልቲ ሚዲያ መልዕክት አገልግሎት፤ የቪዲዮና የድምፅ ፋይሎችን ለመላክና ለመቀበል፣ 1 ሺህ 600 ፊደላት የያዘ፣ በርካታ መልዕክቶችን ለተለያዩ ተቀባዮች በአንድ ጊዜ መላክ የሚያስችል እንዲሁም የተላከው መቼ እንደደረሰና እንደተነበበ ለማወቅ ያስችላል ተብሏል።

የድምፅ መልዕክት አገልግሎት ደግሞ፤ ደንበኞች በተለያየ ምክንያት ጥሪ መቀበል በማይችሉበት ጊዜ ደዋዮች በድምፅ የተቀረፀ መልዕክት እንዲያስቀምጡ በማድረግ፤ በተመቻቸው ጊዜ የተቀመጠላቸውን የድምፅ መልዕክት እንዲያዳምጡ የሚያስችል አገልግሎት ነው።

የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ፤ ኩባንያው የደንበኞቹን የቴክኖሎጂና የዲጂታል ፍላጎቶችን በማሟላት የላቀ ተሞክሮ ማረጋገጥ የሚያስችሉ ዘመን አፍራሽ አገልግሎቶችን እያስተዋወቀ እንደሚገኝም ገልፀዋል።

ኩባንያው ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ጥረት እያደረገ ይገኛል ብለዋል።

ዛሬ ይፋ የሆኑት አዳዲስ አገልግሎቶች በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቁ ላደረጉ የዘርፉ ባለድርሻ አካላትም ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም