ቀጥታ፡

የመንግሥት አገልግሎትን ዲጂታላይዝድ በማድረግ ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለው አሰራር ለማስፈን እየተሰራ ነው

ባህር ዳር ፤ ታህሳስ 5/2016( ኢዜአ)፡- የመንግሥት አገልግሎትን ዲጂታላይዝድ በማድረግ ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለው አሰራር ለማስፈን እየሰራ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ። 

ሚኒስቴሩ በአዲስ አበባ የጀመረውን የዲጂታላይዜሽን ፕሮጀክት ወደ ባህር ዳር የሚያሰፋበት መረሃ ግብር አካሂዷል። 

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ይሹሩን ዓለማየሁ በወቅቱ እንዳሉት፤  ዲጂታላይዜሽን የዓለም የሥልጣኔ መለኪያ ሆኖ እያገለገለ ነው።

በዚህም በአዲስ አበባ ተተግብሮ ውጤታማ የሆነውን “የንግድ ሥራ ቅልጥፍና ማሻሻያ ፕሮጀክት” ወደ አዳማ፣ ድሬዳዋና ባህር ዳር ከተሞች እያስፋፋ መሆኑን ገልጸዋል።

ዓላማውም ዜጎች ባለቡት ሆነው በኢንተርኔት በታገዘ መልኩ ማንኛውንም የመንግሥት አገልግሎት በእኩልነትና በፍትሃዊነት ለመስጠት መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል። 

በዚህም በከተሞች የሚገኙ ተቋማት እርስ በእርሳቸውና ከአገር አቀፍ የመረጃ ቋት በማገናኘት ማንኛውንም መረጃ በየትኛውም አካባቢ ለሚገኙ ለተገልጋዮች ተደራሽ ለማድረግ ነው ብለዋል።

ዲጂታላይዜሽን አገሮች በዓለም ንግድ ድርጅት የሚለኩበት ዋና መለኪያ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በሚኒስቴሩ የኤሌክትሮኒክስ መንግሥት ልማት ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ኢንጂነር አብዮት ሲናሞ ናቸው። 

የንግድ ሥራ ማስጀመር፣ የታክስ ክፍያ፣ የግንባታና ንግድ ፈቃድ፣ የግዥ፣ የገቢና ሌሎችም   በኢንተርኔት ታግዞ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ፕሮጀክት ወደ ትግበራ መግባቱንም አስረድተዋል።

ይህም የደንበኞችን ጊዜ፣ ጉልበትና ገንዘብ በመቆጠብ በመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ እርካታ ለመፍጠር እንደሚያስችል ዋና ሥራ አስኪያጁ አብራርተዋል። 

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተማ ልማት ዘርፍ አስተባባሪና የአማራ ክልል የከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አህመዲን መሐመድ በበኩላቸው፤ በክልሉ የሚገኙ 682 ከተሞችን ወደ ዲጂታል ሥርዓት ለማስገባት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። 


 

በተያዘው ዓመትም ባህር ዳርን  ጨምሮ ስምንት ከተሞችን ወደ ዲጂታል አሰራር ለማሸጋገር እየተሰራ መሆኑን አመልክተው፣ ይህም ሚኒስቴሩ የጀመረው እንቅስቃሴ የተያዘውን ግብ ለማሳካት እንደሚያስችል ገልጸዋል። 

የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ አስሜ ብርሌ ፤ከተማዋን ወደ ስማርት ሲቲነት ለማሸጋገር ግብረ ሃይል ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።


 

በዘመናዊ የመሠረተ ልማት፣ በኢንዱስትሪ፣ በቱሪዝም፣ በግብርና ሌሎች ኢንቨስትመንት መስኮች በፍጥነት እያደገች የመጣችውን ባህር ዳር ከተማ ዲጂታላይዝ በማድረግ እያደገ የመጣውን ፍላጎት ማርካት ይገባል ብለዋል። 

የከተማ አስተዳደሩ ሚኒስቴሩ ላቀረበው የዲጂታላይዜሽን ፕሮጀክት ትግበራ ተገቢውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ምክትል ከንቲባው አረጋግጠዋል። 

ሚኒስቴሩ ፕሮጀክቱን ወደ ተግባር ለመቀየር  የሥልጠናና ሌሎች ድጋፍ እንደሚያደርግ በመርሃ ግብሩ  ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም