በኢትዮጵያ ደኅንነቱ የተረጋገጠ የአየር ትራንስፖርት ማስፋፋት የሚያስችል ጠንካራ የሲቪል አቪዬሽን ተቋም መገንባት ተችሏል - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ደኅንነቱ የተረጋገጠ የአየር ትራንስፖርት ማስፋፋት የሚያስችል ጠንካራ የሲቪል አቪዬሽን ተቋም መገንባት ተችሏል
አዲስ አበባ ፤ ታህሳስ 5/2016 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ደኅንነቱ የተረጋገጠ የአየር ትራንስፖርት ማስፋፋት የሚያስችል ጠንካራ የሲቪል አቪዬሽን ተቋም መገንባት መቻሉን የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዶክተር ዓለሙ ስሜ ገለጹ።
በአቪዬሽን ዘርፍ የፈጠራ ውጤቶችን ላበረከቱ ግለሰቦችና ተቋማት እውቅና የተሰጠ ሲሆን፤ በውድድሩ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃ ለወጡ ለእያንዳንዳቸው የ100 ሺህ ብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
"ፈጠራ ለአቪዬሽን ልህቀት!" በሚል መሪ ሀሳብ የአቪዬሽን ኢኖቬሽን ኤክስፖ ታኅሣሥ 1 ቀን 2016 ዓ.ም. በይፋ መከፈቱ ይታወሳል።
የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዶክተር ዓለሙ ስሜ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በአቪዬሽን ታሪክ የመጀመሪያዋ የሆነችውን አውሮፕላን በ1921ዓ.ም ገፈርሳ ካሳረፈችበት ጊዜ ጀምሮ ኢንዱስትሪው በየጊዜው እድገት እያሳየ ነው።
በአሁኑ ወቅትም በአፍሪካ በሁሉም መስክ በሚባል ደረጃ ግንባር ቀደም የሆነ አየር መንገድ ባለቤት ሆነናል ብለዋል።
ደኅንነቱ የተረጋገጠ የአየር ትራንስፖርት እንዲስፋፋም የቁጥጥር ሥራውን የሚሰራ ጠንካራ የሲቪል አቪዬሽን መገንባት መቻሉን ጠቁመዋል።
የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት የሀገራችንን ቱሪዝም፣ ንግድ፣ ግብርናና ሌሎች ኢኮኖሚዎችን በመደገፍ ረገድ የማይተካ ሚናውን እየተወጣ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
በአቪዬሽን ቴክኖሎጂ ረገድም በአውሮፕላን፣ በአየር አሰሳ መሳሪያዎች፣ እንዲሁም በአውሮፕላን ማረፊያዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉ ቴክኖሎጂዎችን ጥቅም ላይ አውለናል ብለዋል።
የአቪዬሽን ኢኖቬሽን ኤክስፖ ስኬታማ የአቪዬሽን ቴክኖሎጂ እና የምርምር ሥራዎችን ለማሳደግ ምቹ ዕድል የፈጠረ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡
በዚህም 95 ወጣቶች በጋራና በተናጠል 101 የፈጠራ ውጤቶቻቸውን ማቅረባቸውን ጠቅሰው፤ 34 የግልና መንግሥታዊ ተቋማት የሚያከናውኗቸው ሥራዎችንና የፈጠራ ውጤቶችን አቅርበዋል ብለዋል፡፡
ከእነዚህ መካከል የ55 ወጣቶች የፈጠራ ውጤቶቻቸው ተጨባጭ አገልግሎት መስጠት እስከሚችሉ ድረስ ዘላቂ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ገልፀዋል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር 30፣ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር 12፣ አየር ኃይል 5፣ የስፔስ ሳይንስና ጂኦ-ስፓሻል ኢንስቲትዩት 5፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ደግሞ 3 የፈጠራ ባለሙያዎችን በመቀበል ሁለንተናዊ ድጋፍ ለማድረግ መስማማታቸውን ጠቁመዋል።
እንደ ሀገር በዘርፉ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመዝለቅ አቅምን ማሳደግና የመጠቀም አቅምን ማጎልበት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ዋና ዳይሬክተር ጌታቸው መንግስቴ በበኩላቸው፤ ዕቅዳችን ተወዳዳሪ የሆነ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ መገንባት ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ፈጠራ እና ቴክኖሎጂ የመወዳደር አቅምን ከሚወስኑት መካከል ዋነኞቹ መሆናቸውን ገልጸው፤ ኤክስፖው በዚህ ረገድ ትልቅ አስተዋጽዖ አበርክቷል ብለዋል።
እውቅና ከተበረከተላቸው ወጣቶች መካከል የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲው ዮሴፍ ጀማል በስፔስ ኢንዱስትሪ ብዙ ለመሥራት ትልቅ ተስፋ እንዳለው ገልጿል፡፡
አሁን በፈጠራ የቀረቡ ሥራዎች በቀጣይ ማሻሻያ ብቻ በማድረግ ወደ ሥራ መግባት የሚችሉ መሆናቸውንም አመልክቷል።
ሌላኛው ከደንቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ የመጣው ወጣት አማኑኤል ባልቻ፤ ሥራዎቹን በጀመረበት ሦስት ዓመታት 30 ድሮኖች መሥራት መቻሉን ገልጿል።
እነዚህ ድሮኖች ለተለያዩ አገልግሎቶች ጥቅም ላይ የሚውሉ መሆናቸውንም ገልጿል።