ቀጥታ፡

ጉብኝቱ የኢትዮጵያ አየር ኃይል እየገነባ ያለውን አቅም ለማየት አስችሎናል - የአፍሪካ ሀገራት የአየር ኃይል አዛዦች

አዲስ አበባ ፤ ታህሳስ 5/2016 (ኢዜአ) ፦ የአፍሪካ ሀገራት የአየር ኃይል አዛዦች በኢትዮጵያ አየር ኃይል ያደረጉት ጉብኝት ተቋሙ እየገነባ ያለውን አቅም ለመረዳትና ልምድ ለመቅሰም እንዳስቻላቸው ተናገሩ።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል 88ኛ ዓመት የምስረታ በዓል "በመሥዋዕትነት ሀገርን የዋጀ የኢትዮጵያ አየር ኃይል" በሚል መሪ ኃሳብ ከኅዳር 20 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ እየተከበረ ይገኛል።


 

የመርሃ-ግብሩ አንድ አካል የሆነው የአፍሪካ አየር ኃይል አዛዦች ፎረም ትናንት በቢሾፍቱ መካሄዱ ይታወቃል።

በፎረሙ ላይ የተሳተፉ የአፍሪካ አየር ኃይል አዛዦች የኢትዮጵያ አየር ኃይልን የለውጥ ሥራዎች ትናንት ጎብኝተዋል።

በጉብኝቱ የተሳተፉት የቦትስዋና አየር ኃይል አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ሀንድሪክ ራካንዝዋና፤ የኢትዮጵያ አየር ኃይል የተሟላ አቅም እንዳለው በጉብኘቱ መመልከት መቻላቸውን ገልፀዋል።

ቦትስዋና የአየር ኃይል አብራሪዎቿን በኢትዮጵያ ማሰልጠንን ጨምሮ በዘርፉ ያላትን አቅም ለማሳደግ ከኢትዮጵያ ትምህርት መውሰድ እንደምትፈልግ ተናግረዋል።

የአፍሪካ አየር ኃይሎችን የጋራ አቅም ለማስተባበር የተጀመረው ጥረት አበረታች መሆኑንም አመልክተዋል።

በትብብር በመሥራት ያሉብንን ችግሮችና ፈተናዎች በጋራ የመፍታት አቅማችንን ይበልጥ ማጎልበት ይገባናል ሲሉም ተናግረዋል።

ጉብኝቱ የአፍሪካ አየር ኃይሎችን ትስስር ለማጠናከር እንደሚያግዝ ነው የተናገሩት።


 

የዩጋንዳ አየር ኃይል አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ቻርለስ ኦኪዲ በበኩላቸው፤ በጉብኝቱ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ያለውን የመፈጸም አቅም ማየት መቻላቸውን ገልፀዋል።

ዩጋንዳ ከኢትዮጵያ ጋር በአየር ኃይል ዘርፍ ያላትን ትብብር ማሳደግ እንደምትሻም ተናግረዋል።

አፍሪካ በማደግ ላይ የምትገኝ አህጉር መሆኗንና ዓለም በለውጥ ሂደት ውስጥ እንደምትገኝ ጠቅሰው፤ ወታደራዊ ትብብርን ማጠናከር አስፈላጊ ጉዳይ ነው ብለዋል።

አፍሪካውያን የራሳቸውን አቅም በዘላቂነት መገንባት እንዳለባቸውም ነው ሌተናል ጄኔራሉ የተናገሩት።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል 88ኛ ዓመት የምስረታ በዓል የመዝጊያ ሥነ-ሥርዓት ነገ ይካሄዳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም