የአካባቢያችንን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ እየሰራን ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአካባቢያችንን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ እየሰራን ነው
ደብረብርሀን፤ታህሳስ 5/2016(ኢዜአ)፡- አብሮነታቸውን በማጠናከር የአካባቢያቸውን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ እየሰሩ እንደሚገኙ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የሲያ ደብርና ዋዩ ወረዳ ነዋሪዎች ገለጹ።
የወረዳው ነዋሪዎች በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ውይይት አድርገዋል።
ከውይይቱ ተሳታፊ ዎች መካከል መላከ ሰላም ቀሲስ ድረስልኝ ተሰማ በሰጡት አስተያየት፤በአካቢያቸው ቀደም ሲል ተከስቶ በነበረው የሰላም እጦት በግብርናና በሌሎችም የልማት ስራዎች ላይ ተፅዕኖ አሳድሮ መቆየቱን ተናግረዋል።
በማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ላይም ተቸግረው እንደነበር አውስተው፤ በመከላከያ ሰራዊት ድጋፍ አሁን በአካባቢው ሰላም ሰፍኖ ችግሩ መቃለሉን ገልጸዋል።
በተገኘው ሰላም በመኸር የለማውን ሰብል በመሰብሰብ ላይ እንደሚገኙ ጠቅሰው፤ በአካባቢያቸው ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የበኩላቸውን እየተወጡ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
በመንግስት የቀረበውን የሰላም ጥሪ እንዲሳካ እንደሚደግፉ የተናገሩት ደግሞ አርሶ አደር ሽፈራው መንግስቴ ናቸው ።
የአካባቢዉ ሰላም በዘላቂነት እንዲቀጥል ህብረተሰቡን በማስተባበር የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።
አብሮነታቸውን በማጠናከር የአካባቢያቸውን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ ሲከናወኑ የቆዩትን ስራ መቀጠላቸውን አስተያየት ሰጪዎቹ ገልጸዋል።
ጀግናው የመከላከያ ሰራዊት በከፈለው መስዋእትነት ሰላማቸው መመለሱን የገለጹት አስተያየት ሰጪዎቹ ፤ ከጎኑ በመቆም ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።
የማዕከላዊ ሸዋ ኮማንድ ፖስት አባልና የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መካሻ ዓለማየሁ ባደረጉት ንግግር፤ ከገባንበት ችግር ወጥተን ልማታችንን ማፋጠን አለብን ብለዋል።
በክልሉ መንግስት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ እንዲሳካ የሐይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች ሚናቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
ጫፍ የረገጠ የጽንፈኝነት አካሄድ አገር ያፈርሳል ያሉት ደግሞ የማዕከላዊ ሸዋ ኮማንድ ፖስት አስተባባሪ፣ የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ ኦፕሬሽናል ምክትል አዛዥ ብርጋዴል ጀነራል አበባው ሰይድ ናቸው።
በዞኑ አንኮበር ወረዳ ከጽንፈኞች ጋር አብረው የነበሩ ታጣቂዎች በሰላም ተመልሰውና የተሃድሶ ስልጠና ተሰጥቷቸው ወደ ሰላማዊ ህይወታቸው ተመልሰዋል ብለዋል ።