ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ትክክለኛ የሀገር አለኝታና ኩራት መሆኑን በተግባር አረጋግጧል - ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 5/2016 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ትክክለኛ የሀገር አለኝታና ኩራት መሆኑን በተግባር ማረጋገጡን የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል 88ኛ ዓመት የምስረታ በዓል "በመሥዋዕትነት ሀገርን የዋጀ የኢትዮጵያ አየር ኃይል" በሚል መሪ ሀሳብ ከኅዳር 20 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ይገኛል።

በዛሬው ዕለትም "የጥቁር አንበሳ የአየር ትርዒት" ዋዜማን አስመልክቶ የምክክር መድረክ ተካሂዷል።

በዚሁ ወቅት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ኢትዮጵያ ጠንካራ የመከላከያ ሰራዊት መገንባቷን ተናግረዋል።

በተለይ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በርካታ የሪፎርም ስራዎች መሰራታቸውን ገልጸዋል።

ይህም ሥርዓት በተቀየረ ቁጥር የሚፈርስ ሳይሆን አስተማማኝና ዘላቂ የሆነ መከላከያ እንዲኖር ያስችላል ብለዋል።

ተግባራዊ በተደረጉ የሪፎርም ስራዎችም አስተማማኝና የሀገር ኩራት የሆነ ተቋም መገንባት መቻሉን አንስተዋል።

የመከላከያ ሰራዊቱ በሁሉም ግዳጆች ትክክለኛ የሀገር አለኝታ መሆኑን በተግባር እያረጋገጠ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያን የሚመጥን ሰራዊት መገንባት እንደተቻለ በአየር ኃይል የተወሰደው ውጤታማ የለውጥ ርምጃ ማሳያ መሆኑን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ አየር ኃይልን በቴክኖሎጂ፣ በትጥቅ፣ በሰው ኃይልና በአሰራር ማዘመን እንደተቻለ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል 88ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ሲከበር አየር ኃይሉ የሀገር አቅምና አለኝታነቱ የሚታይበት መሆኑንም ተናግረዋል።
 
የአየር ኃይል የምስረታ በዓል ዝግጅትም ጀግኖች በከፈሉት መሥዋዕትነት እና በትውልድ ቅብብሎሽ ወደ ከፍታ ማማ የደረሰ ተቋም መሆኑን ለማወቅ የሚያስችል ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም