የውጭ ባለሀብቶች የመንግስት ሆቴሎችን ለመግዛት ፍላጎት አሳይተዋል - ኢዜአ አማርኛ
የውጭ ባለሀብቶች የመንግስት ሆቴሎችን ለመግዛት ፍላጎት አሳይተዋል
አዲስ አበባ ፤ ታህሳስ 5/2016 (ኢዜአ) ፦ በርካታ የውጭ ባለሀብቶች በመንግስት ስር የሚገኙ ሆቴሎችን ለመግዛት ፍላጎት ማሳየታቸውን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ አስታወቀ።
የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል ለማዘዋወር ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት በተለያዩ የአገልግሎት ዘርፎች ላይ የግል ባለሃብቶች እየተሳተፉ መሆኑ ይታወቃል።
ቴሌኮሙዩኒኬሽን፣ ሎጅስቲክስ፣ ስኳር ኮርፕሬሽን፣ ሆቴልና ቱሪዝም እንዲሁም ለግሉ ዘርፍ ክፍት ለማድረግ የተለያዩ ስራዎች እየተከናወነባቸው ካሉ ዘርፎች መካከል ይጠቀሳሉ።
ሂልተን፣ ግዮን፣ ገነትና የፍልውሃ አስተዳደር ድርጅት በመንግስት ስር የሚተዳደሩ ሆቴሎች ሲሆኑ ሆቴሎቹ የግሉ ዘርፍ እንዲገዛቸው እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ዋና ስራ አስፈጻሚ አብዱራህማን ኢድ ጣሂር ለኢዜአ እንዳሉት፤ በመንግስት ስር የሚተዳደሩ ሆቴሎችን ትርፋማና ተወዳዳሪ ለማድረግ አሁን ያሉበትን ደረጃ ማሻሻል ተገቢ ነው።
ሂልተንና ጊዮን ሆቴል አሁን ባላቸው ደረጃ ከሌሎች ጋር ተወዳዳሪ ሆነው መቀጠል እንደማይችሉ ጠቅሰው፤ ለዚህ ደግሞ የአገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች እንዲይዙት ኢንቨስትመንት የማፈላለግ ስራ እየተከናወነ መሆኑን አመልክተዋል።
ይህም ሆቴሎቹን ደረጃቸውን በማሻሻል የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጡና ትርፋማ እንዲሆኑ እንደሚያስችላቸው ጠቅሰዋል።
ለሆቴሎቹ የሚፈለገው ኢንቨስትመንት ሆቴሎቹ አሁን ካሉበት አምስትና ስድስት የኮከብ ደረጃን ይዘው አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ የሚያደርግ መሆኑን ነው ዋና ስራ አስፈጻሚው ያስረዱት።
በርካታ የውጭ ባለሀብቶች በመንግስት ስር የሚገኙ ሆቴሎችን ለመግዛት ፍላጎት ማሳየታቸውን ጠቁመዋል።
በቀጣይም የአገልግሎት ዘርፎችን ወደ ግል ለማዘዋወር የተለያዩ ስራዎች በመከናወን ላይ እንደሚገኙም አቶ አብዱራህማን አመልክተዋል።
ይህም ዘርፉን ይበልጥ ለማጠናከርና ተወዳዳሪ ለማድረግ ከማስቻሉም ባለፈ ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል እንደሚፈጥርም ገልጸዋል።
የፍልውሃ አገልግሎት ድርጅት ለበርካታ ዜጎች አገልግሎት እየሰጠ በመሆኑ ከሌሎቹ ሆቴሎች በተለየ የደረጃ ማሻሻያ እንደሚደረግለት አመልክተዋል።
ማሻሻያው ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የሕብረተሰብ ክፍሎችን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን በመጥቀስ።
በቀጣይ መስፈርቱን የሚያሟሉ ባለሃብቶችን የሚያሳትፍ ዓለም አቀፍ ጨረታ ለማውጣት ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝና ጨረታው የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን አሳታፊ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ 26 የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ለማስተዳደርና አዳዲስ ድርጅቶችን ለማቋቋም በቅርቡ መመስረቱ የሚታወስ ነው።