ቀጥታ፡

ኢትዮጵያውያን በማህበረሰባቸው ውስጥ ላሉ ችግሮች አካባቢያዊ መፍትሄ አቅራቢዎች እንዲሆኑ እየተሰራ ነው -ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 5/2016 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያውያን በማህበረሰባቸው ውስጥ ላሉ ችግሮች አካባቢያዊ መፍትሄ አቅራቢዎች እንዲሆኑ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ገለጹ።

በሚኒስትሯ የተመራ የኢትዮጵያ ልዑክ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተለያዩ ድርጅቶች ጋር እየመከረ ነው።

በምክክሩ ላይም ዩኒሴፍ ኢትዮጵያ የጀመረችውን ይህንን ስራ እንዲደግፍ የጠየቁት ሚኒስትሯ ፕሮግራሙ ድጋፍ በሚያስፈልጋቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ ትርጉም ያለው ለውጥ ለማምጣት እንደሚያስችል አብራርተዋል።

የዩኒሴፍ ዋና ዳይሬክተር የኢትዮጵያ መንግስት በሴቶችና ህጻናት ህይወት ላይ አዳዲስ ለውጦችን ለማምጣት እያደረገ ያለውን ጥረት አድንቀው እንቅስቃሴውን ለመደገፍ ተቋማቸው ፍላጎት እንዳለው አረጋግጠዋል።

መቀመጫውን ቨርጂኒያ ያደረገው አሊያንስ ኬር ናው የተሰኘ የበጎ አድራጎት ድርጅት ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ለማገዝ በሚደረው እንቅስቃሴ ውስጥ እየተሳተፈ እንደሚገኝ ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም