የሀገር መከላከያ ሠራዊት ብርቅዬ ኢትዮጵያውያን በከፈሉት ውድ መሥዋዕትነት በጽኑ መሰረት የተገነባ ታላቅ ተቋም ነው - ጀኔራል አበባው ታደሰ - ኢዜአ አማርኛ
የሀገር መከላከያ ሠራዊት ብርቅዬ ኢትዮጵያውያን በከፈሉት ውድ መሥዋዕትነት በጽኑ መሰረት የተገነባ ታላቅ ተቋም ነው - ጀኔራል አበባው ታደሰ
አዲስ አበባ ፤ ታህሳስ 5/2016(ኢዜአ)፦ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ብርቅዬ ኢትዮጵያውያን በከፈሉት ውድ መሥዋዕትነት በጽኑ መሰረት የተገነባ ታላቅ ተቋም መሆኑን የኢፌዴሪ የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀኔራል አበባው ታደሰ ገለጹ።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል 88ኛ ዓመት የምስረታ በዓል "በመሥዋዕትነት ሀገርን የዋጀ የኢትዮጵያ አየር ኃይል" በሚል መሪ ሀሳብ ከኅዳር 20 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ይገኛል።
በዛሬው ዕለትም የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀኔራል አበባው ታደሰ፣ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል ይልማ መርዳሳን ጨምሮ የሠራዊቱ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች እና የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ቢሾፍቱ ከተማ የሚገኘውን የአየር ኃይል መኮንኖች ክበብ መርቀው ከፍተዋል።
በመቀጠልም 88ኛው የአየር ኃይል ምስረታ በዓል "የጥቁር አንበሳ የአየር ትርዒት" ዋዜማን አስመልክቶ በአየር ኃይል መኮንኖች ክበብ የምክክር መድረክ እየተካሄደ ይገኛል።
በዚሁ ወቅት የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀኔራል አበባው ታደሰ የመከላከያ ሠራዊት 116ኛ ዓመት በዓል እና የአየር ኃይል 88ኛ የምስረታ ቀን በዓል መከበር ኢትዮጵያ በትውልድ ቅብብሎሽ እዚህ የደረሱ ታላላቅ ተቋማት ያሏት አገር መሆኗን ያሳያል ብለዋል።
የአገር መከላከያ ሠራዊት እንደተቋም በጽኑ መሰረት የተገነባ፣ በስኬት እና በብቃት እየተመራ ያለ የአገር መከታ እና ባለውለታ የሆነ ተቋም መሆኑንም ተናግረዋል።
የመከላከያ ሠራዊት በትውልድ ቅብብሎሽ እዚህ ሲደርስም ብርቅዬ ኢትዮጵያውያን ውድ ህይወታቸውን በመገበር በከፈሉት መሥዋዕትነት መሆኑንም ገልጸዋል።
የሀገር መከላከያ ሠራዊት በርካታ ዓመታትን አልፎ እዚህ ሲደርስ ብርቅዬ ኢትዮጵያውያን በከፈሉት ውድ መሥዋዕትነት በጽኑ መሰረት የተገነባ ተቋም መሆኑን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል ይልማ መርዳሳ በበኩላቸው የአየር ኃይል አመሰራረት እና ታሪካዊ ዳራን በሚመለከት የውይይት መነሻ ጽሁፍ አቅርበዋል።
ቀጥሎም የመድረኩ ተሳታፊ የሠራዊቱ ከፍተኛ መኮንኖች እና የመንግስት የስራ ኃላፊዎች የኢትዮጵያ አየር ኃይል ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ የተገነቡ የውጊያ መሠረተ ልማቶች፣ የትጥቅ አቅም፣ የልማት ስራዎችን እና የተወሰዱ የለውጥ ርምጃዎችን ይጎበኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በትናንትናው ዕለት 88ኛ ዓመት የኢትዮጵያ አየር ኃይል የምስረታ በዓልን በማስመልከት የአፍሪካ አየር ኃይል አዛዦች የምክክር መድረክ ተሳታፊዎች፣ የአፍሪካ ሀገራት አየር ኃይል አዛዦች፣ የአቪየሽን ተቋማት ኃላፊዎችና ወታደራዊ አታሼዎች የኢትዮጵያ አየር ኃይል የገነባውን የውጊያ መሠረተ ልማት፣ የትጥቅ አቅምን እና የተወሰዱ የለውጥ ርምጃዎች መጎብኘታቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል በንጉስ ኃይለ ስላሴ ዘመነ መንግስት የተመሠረተበትን ኅዳር 20 ቀን 1928 ዓ.ም መነሻ በማድረግ 88ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን ለተከታታይ ቀናት በልዩ ልዩ ዝግጅቶች እያከበረ ሲሆን፥ ታኅሳስ 6 ቀን 2016 ዓ.ም የበዓሉ የማጠቃለያ መርሐ-ግብር ይካሄዳል።