ቀጥታ፡

በኮንስትራክሽን ዘርፍ የሚያጋጥሙ ተግዳቶሮችን መፍታት የሚያስችል የሦስትዮሽ ሥምምነት ተፈረመ

አዲስ አበባ ፤ ታኀሳስ 4/2016 (ኢዜአ) ፡- በኮንስትራክሽን ዘርፍ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን በመፍታት ዘርፉ ለአገሪቱ ምጣኔ ኃብታዊ እድገት የሚያበረክተውን አስተዋጽዖ ማጠናከር የሚያስችል የሦስትዮሽ ሥምምነት ተፈረመ።

የሦስትዮሽ ሥምምነቱን የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለሥልጣን፣ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩትና የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች ማኅበር ፈርመውታል።

የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር መስፍን ነገዎ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ የግንባታ ዘርፉ ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ዕድገት ያለውን ድርሻ ለማሳደግ በትብብርና በቅንጅት መሥራት ያስፈልጋል።


 

በኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ዘርፉ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገና ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል እየፈጠረ መሆኑን አንስተው በዘርፉ የሚስተዋሉ የሥነ-ምግባር ጥሰቶችንና የአቅም ውስንነትን በትብብር ለመፍታት ሥምምነቱ ወሳኝ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ተቋራጮች ማኅበር ፕሬዝዳንት ኢንጂነር ግርማ ኃብተማርያም በበኩላቸው፤ የሦስትዮሽ ሥምምነቱ በዘርፋ ያለውን ውድድር ጤናማና ውጤታማ ለማድረግ በማለም የተፈረመ መሆኑን ጠቁመዋል።


 

በተለይም ሥራ ተቋራጮች የግንባታ ሥራዎችን በተያዘለት የጊዜ ገደብ፣ በተመደበለት በጀት እንዲሁም ሙያዊ ሥነ-ምግባርን በጠበቀ መልኩ እንዲያጠናቅቁ አሰሪዎችም ሕግና ሥርዓትን እንዲከተሉ ለማስቻል ሥምምነቱ ትልቅ አስተዋጽዖ ያደርጋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ታምራት ሙሉ፤ ሥምምነቱ የግንባታ ዘርፋ ተወዳዳሪና ሰፊ የሥራ ዕድል እንዲፈጥር የትብብር ሥራዎች እንዲጠናከሩ ያስችላል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም