ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የአፍሪካ አገራት የአየር ኃይል አብራሪዎችና ቴክኒሺያኖችን በማሰልጠን በዘርፉ የካበተ ልምድ አዳብራለች

አዲስ አበባ ፤ ታህሳስ 4/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የተለያዩ የአፍሪካ አገራት የአየር ኃይል አብራሪዎችና ቴክኒሺያኖችን አሰልጥኖ በማብቃት የረዥም ጊዜ ልምድ ማካበቷን የኢትዮጵያ አየር ኃይል ገለጸ። 

የኢትዮጵያ አየር ኃይል 88ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል "በመስዋዕትነት ሀገርን የዋጀ፤ የኢትዮጵያ አየር ኃይል" በሚል ከኅዳር 20 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ እየተከበረ ይገኛል።

ይህንንም ተከትሎ የመጀመሪያው የአፍሪካ አየር ኃይል አዛዦች ፎረም በቢሾፍቱ ተካሂዷል።

በኢትዮጵያ አየር ኃይል ምክትል አዛዥ ለአቪዬሽን ከባድ ጥገና ማዕከል ኮሎኔል መሠረት ጌታቸው በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ የአየር ኃይል 88ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል በተለያዩ መርኃ-ግብሮች እየተከበረ ነው።

ከመርኃ-ግብሮቹ መካከል የአፍሪካ አየር ኃይሎች አዛዦች ፎረም አንዱ መሆኑን ገልጸው፤ ፎረሙ በአፍሪካ በዘርፉ ያለውን ችግር በጋራ ተወያይቶ የመፍትሔ ኃሳብ ለማመንጨት ያለመ ነው ብለዋል። 

በአፍሪካ አገራት የአየር ኃይል ዘርፍ ያለው ችግር ተመሳሳይ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለተመሳሳይ ችግር የተናጠል መፍትሔ ከማፈላለግ ይልቅ በጋራ ተወያይቶ የጋራ መፍትሔ ማስቀመጥ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።  

ኢትዮጵያ ከቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመነ-መንግሥት ጀምሮ የተለያዩ የአፍሪካ አገራትን የአየር ኃይል አብራሪዎችና ቴክኒሺያኖችን የማሰልጠን የካበተ ልምድ እንዳዳበረች ተናግረዋል። 

ኢትዮጵያ በዘርፉ ያላትን የረዥም ጊዜ የካበተ ልምድ የተገነዘቡ የአፍሪካ አገራት ለአየር ኃይሎች ችግር የጋራ መፍትሔ ለመፈለግ ከኢትዮጵያ ጋር ለመተባበር ከፍተኛ ዝግጁነት ማሳየታቸውን ገልፀዋል። 

ኢትዮጵያ በአውሮፕላን ጥገና፣ ባለሙያዎችን በማብቃት ያላትን ልምድ ለመጠቀም ዛሬም ብዙ የአፍሪካ አገራት ጥያቄ እያቀረቡ መሆኑን ጠቁመዋል። 

የኢትዮጵያ አየር ኃይል የውጭ አብራሪዎችን በማሰልጠን ለአገራቸው ችግር ፈቺ ቴክኒሺያኖች እንዲሆኑ ማስቻሉን የገለጹት፤ ኮሎኔል መሠረት፤ የእውቀትና የቴክኖሎጂ አቅም ያላቸውን ባለሙያዎች በማፍራት ጠንካራ የጥገና ማዕከል ገንብተናል ብለዋል። 

ለዚህ ደግሞ አውሮፕላኖችን በራሳችን አቅም ሥልጠና በሰጠናቸው ባለሙያዎች መጠገንና ሥራ ላይ ማዋል በመቻላችን ነው ሲሉ አስረድተዋል።  

ፎረሙም በዘርፉ የተሻለ ትብብርና ቅንጅታዊ አሠራር በመፍጠር ረገድ ስኬታማ መሆኑን ተናግረዋል።  

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም