ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለሥልጣን በዘርፉ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለመፍታት የሚያስችል ስምምነት ተፈራረመ

አዲስ አበባ ፤ ታህሳስ 4/2016 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለሥልጣን በኮንስትራክሽን ዘርፉ ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን በትብብር መፍታትና ለአገር ዕድገት ያለውን ፋይዳ ማሳደግ የሚያስችል የሦስትዮሽ ስምምነት ተፈራርሟል።

ስምምነቱን የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለሥልጣን፣ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት እና የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች ማኅበር ፈርመውታል።

የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር መስፍን ነገዎ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ የግንባታ ዘርፉ ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ዕድገት ያለውን ድርሻ ለማሳደግ በትብብርና በቅንጅት መሥራት ያስፈልጋል።

የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ታምራት ሙሉ፤ ስምምነቱ የግንባታ ዘርፍ ተወዳዳሪና ሰፊ የሥራ ዕድል እንዲፈጥር ከባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ መሥራት ተገቢ ነው ብለዋል።

ኢንስቲትዩቱ ሥራ ተቋራጮች በእውቀትና በቴክኖሎጂ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የአቅም ግንባታ ሥልጠና ይሰጣል ብለዋል።

በዘርፉ የሚስተዋለውን ብልሹ አሠራርና የስነ-ምግባር ጉድለት በመከላከል ዘርፉን ከፉክክር ወደ ውድድር ለመቀየር በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ተቋራጮች ማኅበር ፕሬዝዳንት ኢንጂነር ግርማ ኃብተማርያም በበኩላቸው፤ የሦስትዮሽ ስምምነቱ በዘርፉ ያለውን ውድድር ጤናማና ውጤታማ ለማድረግ ያስችላል ብለዋል።

ማኅበሩ ከ30 ዓመታት በላይ ልምድ ያለው መሆኑን ጠቅሰው፤ ስምምነቱ ይህን ልምድ የበለጠ ለማሳደግ የሚያስችለውን አቅም ለመገንባት ያስችለዋል ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም