የኢትዮጵያ አየር ኃይል በፓን-አፍሪካኒዝም እሳቤ ከአፍሪካ አገራት ጋር በትብብር ሲሰራ ቆይቷል - ዶክተር አብርሃም በላይ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር ኃይል በፓን-አፍሪካኒዝም እሳቤ ከአፍሪካ አገራት ጋር በትብብር ሲሰራ ቆይቷል - ዶክተር አብርሃም በላይ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 4/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አየር ኃይል በፓን-አፍሪካኒዝም እሳቤ ከአፍሪካ አገራት ጋር በትብብር ሲሰራ መቆየቱን የመከላከያ ሚኒስትሩ ዶክተር አብርሃም በላይ ገለጹ።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል 88ኛ ዓመት የምስረታ በዓል "በመስዋዕትነት ሀገርን የዋጀ፤ የኢትዮጵያ አየር ኃይል" በሚል ከኅዳር 20 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ እየተከበረ ይገኛል።
ይህንንም ተከትሎ የመጀመሪያው የአፍሪካ አየር ኃይል አዛዦች ፎረም በቢሾፍቱ ተካሂዷል።
የመከላከያ ሚኒስትሩ ዶክተር አብርሃም በላይ በዚሁ ጊዜ፤ መድረኩ በአፍሪካ በዘርፉ የጋራ ራዕይ ዙሪያ እንዲሁም የአፍሪካውያን ትብብር ለማጎልበት በሚደረገው ጥረት ላይ ለመምከር መልካም አጋጣሚ የፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።
በአህጉሪቷ ቀደምት የሆነው የኢትዮጵያ አየር ኃይል ባለፈባቸው ዓመታት ዘርፈ-ብዙ አቅሞችን እያጎለበተ መምጣቱን አውስተው፤ አየር ኃይሉ የአፍሪካ አቪዬሽን ፋና ወጊ ለሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ መነሻ ማዕከል መሆኑንም ገልፀዋል።
አየር ኃይልን በቴክኖሎጂ፣ በፈጠራና በጥናት ለማዘመን ትኩረት ተሰጥቷል ብለዋል።
ኢትዮጵያ እንደ አገር እንዲሁም አየር ኃይሉ እንደ ተቋም ለፓን-አፍሪካዊ መንፈስ የጋራ ትብብር እንዲጎለብት በቁርጠኝነት ሲሰራ መቆየቱን ጠቁመዋል።