የአፍሪካ ሀገራት አየር ኃይል አዛዦች የኢትዮጵያ አየር ኃይል ያስገነባቸውን የውጊያ መሠረተ-ልማቶች ጎበኙ - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ ሀገራት አየር ኃይል አዛዦች የኢትዮጵያ አየር ኃይል ያስገነባቸውን የውጊያ መሠረተ-ልማቶች ጎበኙ
አዲስ አበባ ፤ ታህሳስ 4/2016 (ኢዜአ)፡- የአፍሪካ ሀገራት አየር ኃይል አዛዦች እንዲሁም የሀገራት የአቪየሽን ተቋማት ኃላፊዎች የኢትዮጵያ አየር ኃይል ያስገነባቸው የውጊያ መሠረተ-ልማቶች እንዲሁም የትጥቅ አቅምን ለማሳደግ የተከናወኑ የለውጥ ስራዎችን ጎብኝተዋል።
"በመስዋዕትነት ሀገርን የዋጀ የኢትዮጵያ አየር ኃይል" በሚል መሪ ሀሳብ የኢትዮጵያ አየር ኃይል 88ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል ከኅዳር 20 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ የአየር ምድቦችና ሁነቶች እየተከበረ ይገኛል።
የመርሐ ግብሩ አካል የሆነ የመጀመሪያው የአፍሪካ አየር ኃይል አዛዦች የምክክር መድረክ(ፎረም) የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳን ጨምሮ የአፍሪካ ሀገራት አየር ኃይል አዛዦች፣ የተለያዩ ሀገራት የአቪየሽን ተቋማት ኃላፊዎችና ወታደራዊ አታሼዎች በተገኙበት ተካሂዷል።
የመድረኩ አላማ በኢትዮጵያ አየር ኃይል ከለውጡ ወዲህ የተሰሩትን ሥራዎችን ማስተዋወቅና የዘርፉን ሁለትዮሽ ግንኙነት ማጠናከር መሆኑ ተመልክቷል።
ከመድረኩ ጎን ለጎን አየር ኃይሉ ያስገነባቸው የውጊያ መሠረተ-ልማቶች እንዲሁም የትጥቅ አቅምን ለማሳደግ የተሰሩ ሥራዎች ምልከታ ተካሂዷል።
በአየር ኃይሉ ከአገራዊ ለውጡ ወዲህ በሰው ኃይል አቅም ግንባታ፣ የትጥቅ አቅምን በማዘመንና በመሠረተ-ልማት ግንባታ በኩል ሰፊ ሥራዎች መከናወናቸው በጉብኝቱ ተመልክቷል።
በተጨማሪም አየር ኃይሉ በግብርና ልማት እያከናወነ የሚገኘውን ዘርፈ ብዙ ተግባራት ላይ ምልከታ ተደርጓል።
በኢትዮጵያ አየር ኃይል የተመሠረተበትን ኅዳር 20 ቀን 1928 ዓ.ም በመነሻነት ተወስዶ ዘንድሮ 88ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል እየተከበረ ሲሆን ታኅሳስ 6 ቀን 2016 ዓ.ም የበዓሉ የማጠቃለያ መርሐ-ግብር ይካሄዳል።