የአፍሪካ አየር ኃይል አዛዦች ፎረም አህጉራዊ ተልዕኮን ለማሳካት ወሳኝ ነው - የመከላከያ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ አየር ኃይል አዛዦች ፎረም አህጉራዊ ተልዕኮን ለማሳካት ወሳኝ ነው - የመከላከያ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ
አዲስ አበባ ፤ ታህሳስ 4/2016(ኢዜአ)፦ የአፍሪካ አየር ኃይል አዛዦች ፎረም አህጉራዊ ተልዕኮን ለማሳካትና ትብብር ለማጠናከር ወሳኝ መሆኑን የመከላከያ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ ገለጹ።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል 88ኛ ዓመት የምስረታ በዓል "በመስዋዕትነት ሀገርን የዋጀ፤ የኢትዮጵያ አየር ኃይል" በሚል ከሕዳር 20 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ እየተከበረ ይገኛል።
የአየር ኃይል የምስረታ በዓል አካል የሆነው የአፍሪካ አየር ኃይል አዛዦች ፎረም ዛሬ በቢሾፍቱ ተካሂዷል።
የመከላከያ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ የአፍሪካ አየር ኃይል አዛዦች ፎረም አህጉራዊ ተልዕኮን ለማሳካትና ትብብርን ለማጠናከር ወሳኝ ነው ብለዋል።
አየር ኃይሉ ከኢትዮጵያ አልፎ የአፍሪካ ኩራት መሆኑን ገልጸው የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከአፍሪካ ቀዳሚው የአየር ኃይል ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በፎረሙ ከ14 የአፍሪካ አገራት የተወጣጡ አዛዦች እና ልዑካን ጨምሮ የተለያዩ አገራት የአቪዬሽን ተቋማት ኃላፊዎችና ወታደራዊ አታሼዎች ተገኝተዋል።