ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በአየር ኃይል መስክ ያካሄደቻቸው የለውጥ ተግባራት  ከሀገራት ጋር የሚኖረውን የዘርፉን ትብብር የሚያሳድግ ነው-ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ 

አዲስ አበባ ፤ ታህሳስ 04/2016 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ በአየር ኃይል መስክ ያካሄደቻቸው የለውጥ ተግባራት በዘርፉ ከአፍሪካ ሀገራት ጋር የሚኖረውን ትብብር የሚያሳድግ ነው ሲሉ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ገለጹ። 

"በመስዋዕትነት ሀገርን የዋጀ የኢትዮጵያ አየር ኃይል" በሚል መሪ ሀሳብ የኢትዮጵያ አየር ኃይል 88ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል ከኅዳር 20 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ የአየር ምድቦችና ሁነቶች እየተከበረ ይገኛል። 

የዚህ መርኃ-ግብር አካል የሆነ የመጀመሪያው የአፍሪካ አየር ኃይል አዛዦች የምክክር መድረክ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳን ጨምሮ የአፍሪካ ሀገራት አየር ኃይል አዛዦች፣ የተለያዩ  ሀገራት የአቪየሽን ተቋማት ኃላፊዎችና ወታደራዊ አታሼዎች በተገኙበት አካሂዷል። 

በመድረኩ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከምስረታው ጀምሮ አሁን የደረሰበትን ሁለንተናዊ አቅም የሚያሳይ ጽሑፋዊ ገለጻ አቅርበዋል። 

ባቀረቡት ጽሑፋዊ ገለጻ የኢትዮጵያን ምድረ ቀደምትነት እና ለቅኝ ግዛት ያልተንበረከከች ሀገር መሆኗን አውስተዋል። 

በአቬዬሽን ምሥረታ ዘርፍም ኢትዮጵያ  ከአፍሪካ ሀገራት  ቀዳሚ መሆኗን ጠቁመው በአጼ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት የተመሠረተ ታሪካዊ አየር ኃይል ባለቤት መሆኗን ገልጸዋል። 

አየር ኃይሉ በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ለሰላም ማስከበር መሰማራቱንና በታሪክ የሚወሳ ግዳጅ መፈጸሙን ሌተናል ጄኔራሉ አውስተዋል። 

የመንግሥታት መቀያየር አየር ኃይሉ በሚፈለገው ልክ እንዳያድግ ማድረጉን ተናግረው ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ በአየር ኃይል በርካታ የሪፎርም ሥራዎች መከናወናቸውን አስታውቀዋል። 

ተቋማዊ ሪፎርም፣ የሰው ኃይል አቅም ግንባታ፣ የትጥቅ አቅምን ማዘመን፣ የመሠረተ-ልማት ግንባታ እንዲሁም የዘርፉን ትምህርት ተቋማት ማቋቋም በአየር ኃይሉ የተከናወኑ አመርቂ የለውጥ ተግባራት መሆናቸውን ገልጸዋል።

የለውጡ እንቅስቃሴ ለአየር ኃይሉ አዲስ ዘመን የፈጠረ ነው ያሉት ዋና አዛዡ ከቀድሞው በተለየ አዳዲስ ተልኮዎችን ለመወጣትና አስተማማኝ ቁመና ላይ እንዲገኝ አስችሎታል ብለዋል። 

በዚህም የኢትዮጵያ አየር ኃይል ታሪክ እና አመርቂ ውጤት የተመዘገበበት የለውጥ ስራ ከአፍሪካ ሀገራት ጋር የሚኖረውን ትብብር የሚያሳድግ ነው ሲሉ ገልጸዋል። 

የኢትዮጵያ አየር ኃይል የለውጥ ተግባራት በምሳሌነት የሚነሳ ነው ያሉት ዋና አዛዡ አፍሪካውያን በጋራ የሚነሱበት ጊዜው አሁን ነው ለትብብር ስራ አብረን እንነሳ በማለት ጥሪ አቅርበዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም