ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ስብዕናችንን የቀረጸን፣ የአገር ፍቅር ስሜት ያወረሰን ተቋም ነው - የቀድሞ አየር ኃይል አባላት 

አዲስ አበባ ፤ ታህሳስ 04/2016 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ስብዕናችንን የቀረጸን፣ የአገር ፍቅር ስሜት ያወረሰንና ለአገር እንድንኖር መሠረት የሆነን ተቋም ነው ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የቀድሞ አየር ኃይል አባላት ተናገሩ።

የአቪዬሽን ትምህርታቸውን በቀድሞዋ ሶቪዬት ሕብረት የተከታተሉት የአየር ኃይል ጡረተኞች ማኅበር ፕሬዝዳንት ኮሎኔል ያሬድ ሽፈራው፤ በ1977 ዓ.ም ነበር የኢትዮጵያ አየር ኃይልን የተቀላቀሉት።

በወቅቱ አገር ችግር ውስጥ እንደነበረች የሚያወሱት ኮሎኔሉ፤ ትምህርታቸውን እንደጨረሱ በቀጥታ ወደ ግንባር በመሰለፍ በሲስተም ኦፕሬሽንና ሌሎች ኃላፊነቶች አገልግለዋል።

ሌላው የማኅበሩ አባል ማስተር ቴክኒሺያን ዮሐንስ አሰኒ፤ በአጼ ኃይለሥላሴ ዘመነ-መንግሥት ጀምሮ እስከ ደርግ መንግሥት ውድቀት ድረስ ለሩብ ክፍለ ዘመን በበረራ ቴክኒሺያንና ሌሎች ሙያዎች አገልግለዋል።

በጡረታ ላይ የሚገኙት ሁለቱ ባለሙያዎች የሥርዓት ለውጥ መደረጉን ተከትሎ ተቋሙን እንዲለቁ መደረጋቸውን ይናገራሉ። 

ከዘጠኝ ዓመታት በኋላ ግን በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት ጥሪ ሲደረግ ተመልሰው ተቋሙን ዳግም አደራጅተው ድል እንዲመጣ ካደረጉ ባለሙያዎች መካከል ናቸው።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከምስረታው ጀምሮ በዘመናዊ አሠራር እንደተገነባ ገልጸው፤ ተቋሙ የኢትዮጵያን የአየር ክልል በማስጠበቅና እግረኛውን በማገዝ የጦር ሠራዊቱ የጀርባ አጥንት እንደሆነ ይገልጻሉ።

የቀድሞ አየር ኃይል አባላት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ አገር ያገለገሉ፣ በአገር ፍቅር የነደዱ፣ ግዳጃቸውን በብቃትና በጀግንነት የተወጡ የቁርጥ ቀን ልጆች እንደሆኑ ይገልጻሉ። 

አየር ኃይል አባላቱን በኢትዮጵያዊ እሳቤ ያነፀ፣ ለሀገር ፍቅር የሚሰራበትና የሚኖርበት ተቋም በመሆኑ፣ በተቋሙ በማገልገላቸው ትልቅ ኩራት ይሰማናል ብለዋል። 

አየር ኃይል በዕውቀት ባህር ነው የሚሉት አባላቱ፣ የአባላቱ ስብዕናና ማንነት የተቀረጸው በተቋሙ ውስጥ በነበረው እንቅሰቃሴ በመሆኑ እንደ ሁለተኛ ቤታቸው ይቆጥሩታል።

ተቋሙ በኢትዮጵያ ተማሪዎች ዘንድ እንደ ብርቅ የሚታይና የአገር ኩራት የሆነ ተቋም እንደነበር አስታውሰው፤ ዛሬም ዘመኑን የዋጁ ቴክኖሎጂዎችን እየታጠቀ የቀጠለ እንደሆነ አንስተዋል።

ይህም ተቋሙ የቀድሞ ደረጃውን ጠብቆ ራሱን እያዘመነ መቀጠሉን የሚያሳይ እንደሆነ ተናግረዋል።

የቀድሞ አየር ኃይል አባላት ለተቋሙ ካላቸው ፍቅር በመነሳትም ሁልጊዜም እንደ ተጠባባቂ ኃይል ራሳቸውን ቆጥረው፤ ዛሬም ተቋሙን በዕውቀትና ልምዳቸው እንደሚያግዙት አንስተዋል።

የወቅቱ አየር ኃይል የቀድሞ ሠራዊት አባላትን እንደ ቤታቸው ቆጥረው እንዲንቀሳቀሱና እንዲያገለግሉ በማድረጉ ተቋሙ እንደ ባለውለታ እንደሚቆጥሩት ገልጸው፤ ማኅበራቸው ከተቋሙ ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም