ኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀሏ ከብራዚል ጋር ያላትን የቀደመ ግንኙነት ያጠናክራል - አክሊሉ ታደሰ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀሏ ከብራዚል ጋር ያላትን የቀደመ ግንኙነት ያጠናክራል - አክሊሉ ታደሰ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 4/2016(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀሏ ከብራዚል ጋር ያላትን የቀደመ ግንኙነት በኢንቨስትመንት ለማጠናከር አይነተኛ ሚና ይጫወታል ሲሉ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አክሊሉ ታደሰ ገለጹ።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የተሳተፈበትና በብራዚል ኤምባሲ አማካኝነት የተዘጋጀው የኢትዮ-ብራዚል የንግድና ኢንቨስትመንት ፎረም ተካሄደ።
በፎረሙ የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ አክሊሉ ታደሰ ባደረጉት ንግግር የብራዚል ባለሀብቶች በኢንዱስትሪ ፓርኮችና በድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጠና ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
ዋና ስራ አስፈፃሚው በመልዕክታቸው ኮርፖሬሽኑ በተለይም ለውጪ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት በሰጠው ልዩ ትኩረት የአሰራር ሪፎርሞችን ተግባራዊ በማድረግና ባጠረ ቢሮክራሲ በዘመናዊ መንገድ አገልግሎት በመስጠት ኢንቨስተሮችን እያስተናገደ እንደሚገኝ አሳውቀዋል።
በቅርቡ ኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀሏ ከብራዚል ጋር ያላትን የቀደመ ግንኙነት በማጠናከር ረገድ ጉልህ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።
የብራዚል አምራች ኩባንያዎችና ባለሀብቶች በተለይም በማኑፋክቸሪንግ እና በአግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፍ በኢንዱስትሪ ፓርኮችና በድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጠና በኢንቨስትመንት እንዲሰማሩም ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮ-ብራዚል ትሬድና ኢንቨስትመንት ፎረም በዛሬው እለት በአዲስአበባ በተለያዩ ሁነቶች የተካሄደ ሲሆን በዚሁ ፎረም ላይ የተሳተፉ የብራዚል ከፍተኛ ባለስልጣናትና ልዑኮች በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ይፋዊ ጉብኝት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።