ቀጥታ፡

የመደመር እሳቤ የኢትዮጵያ ብዝኃ የልማት አቅሞችን ጥቅም ላይ በማዋል ረገድ ተጨባጭ ለውጥ እንዲመጣ አድርጓል

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 4/2016(ኢዜአ)፦ የመደመር እሳቤ የኢትዮጵያ ብዝኃ የልማት አቅሞችን ጥቅም ላይ በማዋል ረገድ ተጨባጭ ለውጥ እንዲመጣ አድርጓል ሲሉ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጂጌ ተናገሩ።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ከኢዜአ ጋር በመተባባር ያዘጋጀው የመደመር ጉዞ ፓናል በቦንጋ ከተማ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጂጌ የመደመር እሳቤና አገራዊ ትሩፋቶች በሚል የውይይት መነሻ ኃሳብ አቅርበዋል።

መደመር ከእሳቤነት ባሻገር ወደ ተግባራዊ እንቅስቀሴ በመቀየር በሁሉም ዘርፎች ለውጥ እንዲመዘገብ ማስቻሉን ተናግረዋል።


 

በኢኮኖሚው መስክ ግብርናን ከማዘመን ባሻገር ሌሎች አማራጭ አቅሞችን ወደ ልማት ማስገባት መቻሉን አውስተዋል።

የኢትዮጵያን የቱሪዝም ማዕከል ማድረግ የሚያስችሉ መሰረተ ልማቶች መከናወናቸውን ጠቅሰው፣ የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶችን በዚህ ረገድ ለአብነት አንስተዋል።

ለአገራዊ ችግሮች አገር በቀል መፍትሄ በማበጀት ረገድም የተሻለ ሥራ ማከናወን መቻሉን ጠቁመዋል።

ኅብረ ብሔራዊ ወንድማማችነትን በማጠናከር ትክክልኛ ፌደራሊዝምን እውን ማድረግ መቻሉንም እንዲሁ።

ኮንትሮባንድ፣ የኑሮ ወድነትና ጽንፍ የረገጡ አካሄዶች ወቅታዊ ፈተናዎች መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም