ቀጥታ፡

በአዲስ አበባ የሁነት ቱሪዝምን ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው 


አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 4/2016(ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ የሁነት ቱሪዝምን ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን የአዲስ አበባ  የባህል ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ አስታውቋል፡፡

አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲና መሆኗ የፈጠረላትን የኮንፈረንስ ቱሪዝም ዕድል በአግባቡ ከተጠቀመች ዘርፉን በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ ይቻላል፡፡

ለዚህም የዘርፉን ማነቆዎች  በመፍታት  የቱሪስት ፍሰትን ማሳደግ  እንደሚገባም  የዘርፉ ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡

"የጉባኤ፣ የኮንፍረንስ፣ የማበረታቻ ጉዞና የዓውደ ርዕይ ሁነቶችን ያጠቃለለው 'ማይስ ቱሪዝም' ከተሰራበት ብዙ ርቀት የሚያራምድ ዘርፍ ነው።

ይህን ተከትሎ አዲስ አበባን ከሁነት ቱሪዝም ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችሉ የአቅም ግንባታ ስራዎች በቅንጅት እየተከናወኑ መሆኑን የአዲስ አበባ  የባህል  ኪነ ጥበብና የቱሪዝም ቢሮ አስታውቋል፡፡ 


 

ቢሮው "የማይስ ወይም የሁነት ቱሪዝም" ዕድገት ፤ዕድሎችና ተግዳሮቶች፤ ዓለም አቀፍ ልምዶችና ተወዳዳሪነት በሚል ርዕስ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እያካሄደ ነው፡፡

በቢሮው የቱሪዝም ዘርፍ ምክትል ኃላፊ አቶ ኃፍታይ ገብረእግዚአብሔር እንደገለፁት፤ኢትዮጵያን ከሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ፀጋዎች ባሻገር በሁነት ዝግጅት ላይ ተወዳዳሪ ሊያደርጋት የሚችል አቅም ተፈጥሯል፡፡

በተለይም በአዲስ አበባ የተገነቡ የተለያዩ ፓርኮች ፣የዲፕሎማቲክ ማዕከልነቷ፣ ተፈጥሮዊና ታሪካዊ ቅርሶቿ ለሁነት ቱሪዝም መጠናከር መልካም ዕድል መሆናቸውን ተናግረዋል።

ዘርፉን በአግባቡ መጠቀም ከተቻለ ለውጭ ምንዛሬ ግኝትና ለሥራ ዕድል ፈጠራ ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥር ገልጸዋል።

የቪዛ አገልግሎት ቀልጣፋ ለማድረግ ፣የዘርፉን ባለሙያዎችና ተቋማት አቅም ለማሳደግ እንዲሁም የአዲስ አበባን ገጽታ  ለመገንባት የሚያስችሉ ተጨማሪ ስራዎች አጋዥ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ማይስ ‹‹MICE›› ምህፃረ ቃሉ ሲተነተን ‹‹meeting incentive conference Exhibitions ወይም "በስብሰባና ኮንፈረንስ ላይ የተመሠረተ ቱሪዝም" እንደ ማለት ነው፡፡ 

የዓለም ባንክ ከቱሪዝም ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር አገሪቱ በቱሪዝም መስክ የምታገኘውን ገቢ ለማሳደግ "የማይስ ቱሪዝም" የሚመራበት የአሥር ዓመት ስትራቴጂ ማዘጋጀቱን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

የማይስ ቱሪዝምን ዘርፍ የሚመራው የኢትዮጵያ ኮንቬንሽን ቢሮ ጥቅምት 2013 ዓም ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ በተገኙበት ይፋ መደረጉ ይታወሳል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም