የነቀምቴ አፈር ምርምር ማዕከል የአፈር አሲዳማነትን በመቀነስ የተሻለ ምርት ለማግኘት እየሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የነቀምቴ አፈር ምርምር ማዕከል የአፈር አሲዳማነትን በመቀነስ የተሻለ ምርት ለማግኘት እየሰራ ነው
ነቀምቴ ፤ታህሳስ 04/2016 (ኢዜአ)፦ በምዕራብ የኦሮሚያ ዞኖች ባሉ ወረዳዎች የአፈር ለምነትን በመጨመር የተሻለ ምርት ለማግኘት እየሰራ እንደሚገኝ በኦሮሚያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የነቀምቴ አፈር ምርምር ማዕከል ገልጿል።
በምርምር ማዕከሉ ባለሙያዎች ታግዘው ማሳቸውን በኖራ እና ቬርም ኮምፖስት ማከም የቻሉ አርሶ አደሮች በበኩላቸው ምርታማነታቸው እየጨመረ መሆኑን አንስተዋል።
የአፈር ለምነት መቀነስ ወይም የአፈር አሲዳማነት በአገልግሎት ጊዜ ብዛት፣ በዝናብ የአፈር በጎርፍ መታጠብ እና በሌሎች በርካታ ምክንያቶች እንደሚከሰት የዘርፉ ባለሙያዎች ያነሳሉ።
የአፈር ለምነቱን መልሶ የተሻለ ምርት ለማግኘት ታዲያ የአፈር አሲዳማነት ማከምና የተጎዱ አካባቢዎች እንዲያገግሙ መስራት እንደ መፍትሔ ይነሳል።
በኦሮሚያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የነቀምቴ አፈር ምርምር ማዕከል ሃላፊ አቶ ጫልሲሳ ታከለ እንዳሉት ማዕከሉ በአራቱ የወለጋ ዞኖችና ምዕራብ ሸዋ ውስጥ በዚህ ላይ በስፋት እየሰራ ይገኛል።
ከዚሁ ጎን ለጎን አርሶ አደሩንም ከአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ጋር እንዲተዋወቅና የአፈር ለምነቱ ተጠብቆ ምርት እና ምርታማነትን ለመጨመር ስልጠናዎችን በመስጠትና በድጋፍና ክትትል መልክ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
በተለይም ከሰው ሰራሽ ማዳበሪያ ጎን ለጎን የተፈጥሮ ማዳበሪያ መጠቀም፣ ቨርም ኮምፖስትና ኖራን መጠቀም እንዲሁም ሰብልን በማፈራረቅ ማረስ በሳይንሱ የተደገፈ መፍትሔ መሆኑን አንስተዋል።
የአፈር አሲዳማነት በተለይም በምዕራብ ኦሮሚያ ባሉ ዞኖች ከፍ ብሎ የሚታይ መሆኑን ያነሱት አቶ ጫልሲሳ፤ በዚህም አርሶ አደሩ የማምረት አቅሙን እያጣ በመምጣቱ ይህንን ለመፍታት የምርምር ማዕከላቸው እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
አፈር የማምረት አቅሙ ከቀነሰ ለግብርናው ዘርፍ አስጊ እንደሆነ ገልፀው በሰው ሰራሽ ችግሮች የመጡትን በመከላከል የተፈጥሮ ምክንያቶችን ደግሞ የተለያዩ ምርምሮችን በማድረግ ማሻሻል ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
የምርምር ማዕከሉ በማሳ ላይ ለአርሶ አደሮች ከሚሰጠው ስልጠናና ድጋፍ በተጨማሪ የዞኖቹን የአፈር አይነት በመለየት እና በመመርመር እንዲሁም የደረሰውን ጉዳት አይነት በመለየት ለመፍትሔው ከኢንስቲትዩቱ ጋር እንደሚሰራ ተናግረዋል።
በማዕከሉ የአፈር አሲዳማነት ጉዳይ ተመራማሪ አቶ ተመስጌን ሁንዴሳ በበኩላቸው በምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢዎች የአፈር አሲዳማነት በየጊዜው እየጨመረ በመምጣቱ መንግስት በሰጠው አቅጣጫ መሰረት ለመፍትሔው በስፋት በመስራት ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
የተፈጠረው ችግር አካባቢው ዝናባማ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ መሆኑን ገልፀው አሁን ላይ በኖራ የማከም ስራ በስፋት በመስራት ላይ እንደሚገኙ እና በዚህም ለውጥ እየታየ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በአርጆ ወረዳ ላሎ ይድኔ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ቡልቲ ታደሰ እንዳሉት ከዚህ በፊት መሬታችን በተለያዩ ምክንያቶች በመጎዳቱ በዘራነው ልክ ማግኘት አልቻልንም ብለው ዘንድሮ ግን በተሰጣቸው ምክር እና ድጋፍ መሰረት ሰርተው ለውጥ እያዩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ቀድሞ ከአንድ ሄክታር በአማካይ ከሃያ እና ሰላሳ ኩንታል በላይ ምርት እንደማያገኙ ጠቁመው አሁን ከሃምሳ እስክ ስልሳ ኩንታል የስንዴ ምርት እያገኙ መሆናቸውንም አክለዋል።
ከኢንስቲትዩቱ ጋር በመስራት ላይ የሚገኙ ሌላኛው የይድኔ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር በሊና ጨዋቃ በበኩላቸው በአፈር አሲዳማነት መሬታቸው የማምረት አቅሙ ተዳክሞ እንደነበር ያስታውሳሉ።
አሁን ላይ ግን ከማዳበሪያ በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ እና ኖራ በመጠቀም የተሻለ ምርት ማግኘት መቻላቸውን በማከል።
ለሙከራ ከተሰሩ ስራዎችም ልምድ በመቅሰም አስፍተው ለመስራት ማቀዳቸውን ገልፀዋል።